ስልጠናው በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታትና አሰራሮችን ለማዘመን አቅም እንደሚፈጥር ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ስልጠናው በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታትና አሰራሮችን ለማዘመን አቅም እንደሚፈጥር ተገለጸ
ሆሳዕና ፤ ነሐሴ 23/2016 (ኢዜአ)፡-ለቴክኒክና ሙያ አሰልጣኞች የተዘጋጀው ስልጠና በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታትና አሰራሮችን ለማዘመን አቅም እንደሚፈጥር ተገለጸ።
የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ጋር በመቀናጀት "ብቃት ለቴክኒክና ሙያ ልህቀት" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ስልጠና ከትላንት ጀምሮ በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ እየሰጠ ነው።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የቡታጅራ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አሰልጣኝ መምህር ተስፋዬ አሰግደው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ስልጠናው በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ዘርፍ ያሉትን ማነቆዎች ለመፍታትና አሰራሮችን ለማዘመን ወሳኝነት አለው።
በተለይ ከዚህ ቀደም ከነበረው ልማዳዊ የመማር ማስተማር ዘዴ በማላቀቅ ለዘርፉ ውጤታማነት ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር ጠቅሰው፤ "ይህም ብቃት ያለውና አምራች ዜጎችን በየደረጃው ለማፍራት ያስችላል" ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት ለቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተገቢ ትኩረት ተነፍጓቸው በመቆየቱ የሚጠበቅባቸውን ውጤት ሳያመጡ መቆየታቸውን የገለጹት ደግሞ የወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አሰልጣኝ መምህር ዘይነብ ወርቁ ናቸው።
በዚህም ምክንያት በርካታ ዜጎች ከስራ ፈጣሪነት ይልቅ ስራ ጠባቂ እንዲሆኑ በማድረግ በአገሪቷ ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን አስረድተዋል።
አሁን የተዘጋጀው ስልጠና ችግሩን ለማቃለልና ለዜጎች የስራ ፈጠራ እድሎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመው፤ በመምህራኑ ዘንድም መነቃቃትን እንደሚፈጥር አመልክተዋል ።
"የቴክኒክና ትምህርትና ስልጠና ተቋማት በእውቀትና ክህሎት የበቁ ስራ ፈጣሪ ዜጎችን ማፍራት የተሰጣቸው አገራዊ ተልዕኮ ነው" ያሉት ደግሞ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር ሰለሞን ፈርሻ ናቸው።
በአገሪቷ የተጀመረውን ሁለንተናዊ የልማትና ብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ በእውቀትና በክህሎት የበለፀገ የሰው ኃይል መፍጠር ከተቋማቱ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
በመሆኑም ስልጠናው በክህሎት የበለፀጉ ዜጎችን በማፍራት ረገድ ያለውን የአመለካከት ውስንነቶችን በማቃለል ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት የሚያግዝ እንደሆነ አስረድተዋል።
የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት አሰልጣኞችን ቴክኒካዊ የመማር ማስተማር ስነ ዘዴንና ባህሪያዊ ብቃትን በማሳደግ በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ የስልጠናው ዓላማ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቴክኒክና ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ያላቸውን እምቅ አቅም ተጠቅመው የራሳቸውን ገቢ እንዲያመነጩ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አክለዋል።
ያሉባቸውን ማነቆዎች በመፍታት ከገቢ ማመንጫነት በተጨማሪ የስራ እድል ለመፍጠር የሚያግዙ ተቋማት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ለዘርፉ ስኬታማነት አዳዲስ በተቀረፁ ፖሊሲዎችና እሳቤዎች ዙሪያ ለአሰልጣኞቹ ግንዛቤ በመፍጠር በጋራ በመጓዝ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ማጠናከር ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
ለዚህም ስኬት በክልሉ ከሚገኙ 38 የቴክኒክና ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የተውጣጡ ከሁለት ሺህ በላይ ሰልጣኞች ስልጠናውን መውሰድ መጀመራቸውን ተናግረዋል።