የሺ ጋብቻ የሀገሪቱን ባህላዊ እሴቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍና ለማስተዋወቅ ሚናዉ የጎላ ነው-የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2016(ኢዜአ)፦ የሺ ጋብቻ የሀገሪቱን ባህላዊ እሴቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍና ለማስተዋወቅ ሚናው የጎላ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርና የሺ ጋብቻ መርኃ ግብር አዘጋጅ ያሜት ኤቨንት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።


 

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ሸዊት ሸንካ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ስምምነቱ የህዝቦች ባህላዊ እሴቶች እንዲጠናከሩ የሚያስችል ነው፡፡

የሺህ ጋብቻ አያሌ ጥንዶች በአንድ ላይ የሚሞሸሩበትና በየአካባቢው ያሉ ባህሎችና እሴቶች ጎልተው በመውጣት ለዓለም እንዲተዋወቁ ዕድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።

መርኃ ግብሩ ባህላዊ እሴቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ የሚያስችል ከመሆኑ ባለፈ ፤ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ ሁሉም አካል ድጋፍና እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የያሜንት ኤቨንትና የሺ ጋብቻ  አዘጋጅና መስራች አቶ አስናቀ አማኑኤል በበኩላቸው ፤ መርኃ ግብሩ የሀገሪቱን ባህል ለማስተዋቅ፣ የባህል አልባሳት ኢንዱስትሪውን ለማነቃቃትና የተጋቢዎችን ወጪ ለመቀነስ የተጀመረ ፕሮግራም ስለመሆኑ  ተናግረዋል፡፡


 

በ2017 የሺ ጋብቻ ፕሮግራም ከሁሉም ክልሎች ከሚመጡ አንድ ሺ ጥንዶች በተጨማሪ ከአፍሪካ ሀገራት ጭምር ሙሽሮች በራሳቸው ባህል እንዲሳተፉ እየተሰራ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም