ካዌምፔ ሙስሊም ክለብ በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
ካዌምፔ ሙስሊም ክለብ በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቀቀ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2016(ኢዜአ)፦ በ2024/25 የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ የደረጃ ጨዋታ የዩጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊም ክለብ የታንዛንያውን ሲምባ ኩዊንስን 2 ለ 0 በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ውድድሩን አጠናቋል።
በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ የአማካይ ተጫዋቿ ሱማያ ናቡቶ በ19ኛው ደቂቃ ካዌምፔን መሪ ያደረገች ግብ አስቆጥራለች።
የፊት መስመር ተሰላፊዋ አግነስ ናቡኬንያ በ50ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን ግብ ከመረብ አሳርፋለች።
ውጤቱን ተከትሎ ካዌምፔ ሙስሊም ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ውድድሩን አጠናቋል።
የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ የፍጻሜ ጨዋታ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ኬንያ ፖሊስ ቡሌትስ መካከል ከቀኑ 8 ሰዓት በአበበ በቂላ ስታዲየም ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታውን ካሸነፈ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዞንን ወክሎ በ2024/25 የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ይሳተፋል።