የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት 2ኛውን ዙር ሀገር አቀፍ የግብርና ቆጠራ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት 2ኛውን ዙር ሀገር አቀፍ የግብርና ቆጠራ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ ነው
ጋምቤላ ፤ ነሐሴ 23/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት 2ኛውን ዙር ሀገር አቀፍ የግብርና ናሙና ቆጠራ ለማካሄድ ከ43 ሺህ ለሚበልጡ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በዩኒቨርሲቲዎች እየሰጠ መሆኑን አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የተቋማዊ ለውጥ ስራ አስፈፃሚ አቶ አብነት አዋዝ ለኢዜአ እንደገለጹት በ2017ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው 2ኛው ዙር የግብርና ቆጠራ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው።
ሀገር አቀፍ የግብርና ቆጠራው መንግስት ለሚተገብራቸው ልማቶችና ፖሊሲዎች ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን ገልጸው፤ በአጠቃላይ ለሀገሪቷ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው በማከል።
አገልግሎቱ በእስካሁኑ ሂደት የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠቱን፣ የተቆጣጣሪዎች ቅጥር ማካሄዱንና ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ከ43 እስክ 45 ሺህ የሚደርሱ የመረጃ ሰብሳቢዎች ምልመላ ማካሄዱን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በሀገሪቷ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ከነሐሴ 16 ቀን 2016ዓ.ም ጀምሮ ለመረጃ ሰብሳቢዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በአገልግሎት መስሪያ ቤቱ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ዱባለ ከበደ በበኩላቸው ለአንድ ዓመት በሚካሄደው ሀገር አቀፍ የግብርና ቆጠራ ሁሉን አቀፍ የግብርና ልማት ስራዎች ይካተታሉ ብለዋል።
በግብርና ቆጠራው ከሚካተቱት መካከል የእርሻ መሬት፣ ለእርሻ ያልለማ መሬት፣ የዳልጋ ከብቶች፣ በግና ፍየሎችን ጨምሮ አጠቃላይ የቤት እንስሳት እንደሚገኙበት ተናግረዋል።
ለመረጃ ሰብሳቢዎችና ተቆጣጠሪዎች ከነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰጠ ያለው ስልጠና እስከ መስከረም 5 ቀን 2017ዓ.ም የሚቆይ መሆኑንም አቶ ዱባለ ገልጸዋል።