ቀጥታ፡

በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለ172 ሺህ    ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል  መፍጠር  መቻሉን  የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ

ሀዋሳ፤ ነሐሴ 23 / 2016 (ኢዜአ)፡- በአምራች ኢንዱስትሪው  ዘርፍ ባለፈው የበጀት ዓመት ለ172 ሺህ   ዜጎች ቋሚ  የስራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን  የኢንዱስትሪ  ሚኒስቴር ገለጸ።

በተያዘው የበጀት ዓመትም የስራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚዎችን ለማሳደግ ልዩ ክትትል እንደሚደረግም  ተመልክቷል። 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ እንደ አገር በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ነው።

በተኪ ምርት፣ በስራ ፈጠራ ትስስርና በሌሎችም ስኬቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ባለፈው የበጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተኪ ምርት በማምረት  የገበያው ድርሻም እያደገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዘሁ ዘመን ዘርፉን ከስራ ዕድል ፈጠራ ለማስተሳሰር በተደረገው ጥረትም ለ172 ሺህ ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል በመፍጠር  ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በአገሪቱ የኢንቨስትመንት ሽፋን እያደገ የመጣ በመሆኑ የስራ ፈጠራ ትስስር እየሰፋ እንደሚሄድም  አመልክተዋል።

ዘርፉ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል የመፍጠር አቅም ያለው መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ አዳዲስ ወደስራ የሚገቡ ኢንዱስትሪዎች በማጠናከር የስራ ዕድል ፈጠራን ለማስፋት ይሰራል ብለዋል።

በ2017 በጀት ዓመት ደግሞ ይህን የስራ ዕድል ፈጠራን ለማሳደግ ልዩ  ክትትል እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ከሰው ሀይል አቅርቦት አንጻር በተለይም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ወጣቶች ለዘርፉ የሚመጥን ክህሎት እንዲጨብጡ  ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል። 


 

የሐረሪ ክልል ኢንተርፕራይዝ ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሀምዲ ሰለሀዲን በበኩላቸው፤ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ከስራ ዕድል ፈጠራ ጋር ለማስተሳሰር ባለፈው የበጀት ዓመት  በተደረገው ጥረት ከ1 ሺህ 200 በላይ ሰዎችን  ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ገልጸዋል። 

በክልሉ ከአገልግሎት ዘርፍ ቀጥሎ በስራ ዕድል ፈጠራ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተው፤  ይህን ለመጠቀም  ነባር ኢንዱስትሪዎች በማጠናከርና አዳዲስ ለመሳብ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

በክልሉ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የስራ ዕድል ፈጠራን ለማበረታታት በርካታ ተግባራት መኖራቸውን የገለጹት ደግሞ የሲዳማ ክልል የኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ አቶ ጎሳዬ ጎዳና ናቸው።  

በዚህም ባለፈው የበጀት ዓመት በተደረገው ንቅናቄ ከ21 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች በክልሉ በተለያየ ደረጃ ባሉት ኢንዱስትሪዎች የስራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

ዘርፉ ያለውን አቅም በእውቀት ላይ ተመስርቶ ለመጠቀም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር  በመተባበር አጭጭር ስልጠናዎች ለማመቻቸት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ግዛው ጋጊያብ በበኩላቸው፤ በክልሉ በሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ3 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች  የስራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ እንደሆኑ አውስተዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለውን ሰፊ የስራ ዕድል የመፍጠር አቅም ለመጠቀም እየሰራን ነው ብለዋል። 

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ በሀዋሳ ከተማ ምክክር ማካሄዱ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም