በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህገ ወጥ መድኃኒቶችና ምግቦችን በመቆጣጠር ረገድ የተሻለ ውጤት ተገኝቷል - የኢትዮጵያ የምግብ እና የመድኃኒት ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህገ ወጥ መድኃኒቶችና ምግቦችን በመቆጣጠር ረገድ የተሻለ ውጤት ተገኝቷል - የኢትዮጵያ የምግብ እና የመድኃኒት ባለስልጣን
ድሬዳዋ ፤ ነሐሴ 23/2016 (ኢዜአ)፡- በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህገ ወጥ መድኃኒቶችና ምግቦችን በመቆጣጠር ረገድ የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ተግባራት በማከናወን ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ የምግብ እና የመድኃኒት ባለስልጣን ተናገረ።
በምግብና ጤና ግብዓት ቁጥጥር ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራትና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ የሚመክር የኢትዮጵያ የምግብ እና የመድኃኒት ባለስልጣን ዓመታዊ ጉባዔ በድሬዳዋ ተጀምሯል።
ጉባዔውን ያስጀመሩት የባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሂራን ገርባ እንዳሉት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህገ ወጥ መድኃኒትና ቁጥጥርን በተቀናጀ መንገድ በመከላከል ረገድ አበረታች ስራዎች ተሰርተዋል።
የምግብ ደህንነትና ጥራት እንዲረጋገጥ የተሰሩ ስራዎችም የተሻለ ውጤት ተገኝቶባቸዋል ብለዋል።
ወጥ እና ደረጃውን የጠበቀ የቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት፣ ቅንጅታዊ ስራን በማጠናከር የተሻለ ስራ ለመስራት የሚያስችሉ ቅደመ ዝግጅቶች መከናወናቸውንም አክለዋል።
እነዚህን ስራዎች በተቀናጀ እና በተናበበ ስራ በማስቀጠል የተሻለ ለውጥ ለማምጣት በድሬዳዋ የተጀመረው ዓመታዊ ጉባዔ ጥሩ መደላድል እንደሚፈጥርም አውስተዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዩሱፍ ሰኢድ በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህገ ወጥ መድኃኒቶች እና ምግቦችን በመቆጣጠር እና ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ረገድ አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ህገ ወጥ መድኃኒቶች ሲያሰራጩ በተገኙት ላይ እርምጃ በመወሰድ እና የህብረተሰቡን ጤና በመጠበቅ ረገድ አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን ነው የገለፁት።
ውጤቶቹ የተገኙት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ከፌደራልና አጎራባች ክልሎች ተቋማት ጋር በተቀናጀ እና በተናበበ መንገድ በመሰራቱ ነው ብለዋል።
በቀጣይም ቢሮው በዳይሬክቶሬት ደረጃ ያለውን የቁጥጥር አደረጃጃት ወደ ባለስልጣን ከፍ በማድረግ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅት ማጠናቀቁን ተናግረዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው ዓመታዊ የግምገማ ጉባዔ ላይ በዘርፉ ትኩረት በተሰጣቸው ስድስት ዋና ዋና ተግባራት ላይ ውይይት እንደሚካሄድ ተመልክቷል።
በጉባዔው ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ የሁሉም ክልሎች የጤና ቢሮና የዘርፉ የአመራር አካላት እንዲሁም የጉምሩክ ኮሚሽን እና የፌደራል ፖሊስ አመራር ተሳታፊ ሆነዋል።