ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለዜጎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ሊሰሩ ይገባል - ትምህርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለዜጎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ሊሰሩ ይገባል - ትምህርት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2016(ኢዜአ)፦ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለዜጎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ሊሰሩ እንደሚገባ ትምህርት ሚኒስቴር አሳሰበ።
"ፍትሕዊና ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም" በሚል መሪ ሃሳብ 33ኛው የትምህርት ጉባኤ የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ መድረክ በአዲስ አበባ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔ፥ መንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተደራሽነትን ከማስፋት በተጓዳኝ ለትምህርት ጥራትና ፍትሕዊነት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሚያከናውኑት የጥናትና ምርምር ስራ የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል እያገዙ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለዜጎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ምቹ የመማር ማስተማር ምኅዳርን መፍጠር የሚያስችል ተቋማዊ ሥርዓትና ሁኔታን መፍጠር እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚታዩ የመሠረተ ልማት ጉድለቶችን ለማሟላት በሚደረገው ጥረት ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ፥ ተቋማቸው በ1988 ዓ.ም ስራ ከጀመረ ጀምሮ ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ለመንግስት ሠራተኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ለሀገር ዕድገትና ብልጽግና ገንቢ ሚና እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም ለመንግስት ግዥ ሥርዓት መዘመን፣ ለዴሞክራሲ ሥርዓት መጎልበት፣ ለፍትሕና የዳኝነት አገልግሎት መሻሻል የበኩሉን ሚና መጫወቱን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም በከተማ ልማትና ሌሎች ወሳኝ መስኮች ትምህርትና ስልጠና በመስጠት ተልዕኮውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም ከተለያዩ ሀገራት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር የሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ የቅበላ አቅሙን በማሳደግ ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ይሰራል ብለዋል።
የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃጸምና የ2017 ዓ.ም ዕቅድ ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተገልጿል፣፣
በተጨማሪም የአካዳሚክ ጉዳዮች፣ የምርምርና የማኅበረሰብ ጉድኝት፣ የአይሲቲ እና የዲጂታል ትምህርት፣ የአስተዳደርና መሠረተ ልማት፣ የሪፎርም ስራዎችን ጨምሮ የቁልፍ አፈፃጸም አመላካች ጉዳዮችን የሚዳስሱ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር እየተደረገባቸው ይገኛል።
በ33ኛው የትምህርት ጉባኤ የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ መድረክ ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዝዳንቶችና የትምህርት ዘርፍ ልማት ተዋናዮች ተገኝተዋል።