ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በቻይና ቤጂንግ በተካሄደ ዓለም አቀፍ ሴሚናር ላይ በዘላቂ ልማት ግቦች ላይ ያላትን ተሞክሮ አካፈለች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2016(ኢዜአ)፦ በቻይና ቤጂንግ በተካሄደ የዘላቂ ልማት ግቦች ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ በዘላቂ ልማት ግቦች ያላትን ተሞክሮ አጋርታለች።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ(ዶ/ር) የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በቻይና ቤጂንግ በተካሄደው የዘላቂ ልማት ግቦች ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ተሳትፏል።

ስብስባው በዓለም አቀፉ የፓርላማ ሕብረት(IPU) እና በቻይናው ብሔራዊ የሕዝብ ኮንግረንስ(NPC) ትብብር የተዘጋጀ ነው።

ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር )የኢትዮጵያን ዘላቂ የልማት ግቦች አፈጻጸምና ምክር ቤቱ ለግቦቹ መሳካት እያደረገ ያለውን ድጋፍና ክትትል የተመለከተ ተሞክሮ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያም አሁን የጀመረችውን አመርቂ የለውጥ ጉዞ በማፋጠን ሕዝቦቿን ወደ ብልፅግና ለማድረስ እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።


 

ኢትዮጵያ በትክክለኛ የልማት ጎዳና ላይ ያለችና ለሌሎች ሀገራትም ልምድ መቅሰሚያ የምትሆን ሀገር ናት ብለዋል።

ይህን ጅምር በዘላቂነት ለማፅናት የሀገርን ሰላም፣ ክብር እና ብልጽግናን ማስጠበቅ የሁሉ አካል ኃላፊነት እንደሆነ መግባባት እንዲሁም በጋራ መቆምን የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለልማት ጉዞው ታሪካዊና ባህላዊ እሴቷን ጠብቃ ለትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችሉ የልማትና ሌሎች ተግባራት ዕውን ማድረግ የቻለችውን ቻይና ልምድ መቅሰሟን ነው የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ የገለጹት።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር) የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ ከስብስባው ጎን ለጎን የቻይናን የለውጥና የልማት እንቅስቃሴዎች መጎብኝቱን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም