ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሜዳሊያ ያገኙበታል ተብለው የሚጠበቁ የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሜዳሊያ ያገኙበታል ተብለው የሚጠበቁ የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2016 (ኢዜአ)፦ በፔሩ እየተካሄደ ባለው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚጠበቁባቸው ሁለት የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
የሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል የፍጻሜ ውድድር ከሌሊቱ 7 ሰዓት ከ37 ላይ ይደረጋል።
አትሌት ሲምቦ አለማየሁና አትሌት ትዕግስት ገሰሰ ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ።
አትሌት ሲምቦ በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በጣልያን በተደረገ ውድድር 9 ደቂቃ ከ00 ሴኮንድ ከ71 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓት አስመዘግባለች።
አትሌቷ በኮሎምቢያ ካሊ በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና በርቀቱ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ማግኘቷ የሚታወስ ነው።
ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት ፍሬህይወት ገሰሰ በሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም በቻይና ሺያሜን በተካሄደ የዳይመንድ ሊግ ውድድር 9 ደቂቃ ከ25 ደቂቃ
ከ53 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቷን አስመዝግባለች።
በፍጻሜው ውድድር ላይ 16 አትሌቶች ይሳተፋሉ።
ከሌሊቱ 8 ሰዓት ከ17 ላይ የወንዶች 3000 ሜትር የፍጻሜ ውድድር ይካሄዳል። አትሌት ይበልጣል ጋሻውና አትሌት አብርሃ ገብሩ ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ።
አትሌት ይበልጣል 7 ደቂቃ ከ58 ሴኮንድ ከ70 ማይክሮ ሴኮንድ ፣ አትሌት አብርሃ 7 ደቂቃ ከ59 ሴኮንድ ከ00 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓታቸው ሆኖ ተመዝግቧል።
ሁለቱ አትሌቶች የግል ምርጥ ሰዓታቸውን ያስመዘገቡት በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም በሃዋሳ በተካሄደው 12ኛው የኢትዮጵያ ከ20 በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ነው።
ከፍጻሜው በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የማጣሪያ ውድድሮች ይካሄዳሉ።
ከምሽቱ 3 ሰዓት ላይ በሚካሄደው የ3000 ሜትር ሴቶች ማጣሪያ አትሌት አለሺኝ ባወቀና አትሌት ማርታ አለማየሁ ይሳተፋሉ።
አትሌት አለሺኝ 8 ደቂቃ ከ41 ሴኮንድ ከ10 ማይክሮ ሴኮንድ እንዲሁም አትሌት ማርታ 8 ደቂቃ ከ45 ሴኮንድ ከ40 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓታቸው ነው።
በሁለት ምድብ ተከፍሎ በሚደረገው ማጣሪያ ከአንድ እስከ ስምንት የሚወጡ አትሌቶች ለፍጻሜ ያልፋሉ።
ከምሽቱ 5 ሰዓት ከ58 የ800 ሜትር ሴቶች የግማሽ ፍጻሜ ውድድር ይካሄዳል። አትሌት አስቴር አሬሬ በውድድሩ ላይ ትሳተፋለች።
አስቴር 2 ደቂቃ ከ04 ሴኮንድ ከ76 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቷ ነው።
በሶስት ምድብ በሚካሄደው ማጣሪያ ከየምድቡ አንደኛና ሁለተኛ የሚወጡ አትሌቶች በቀጥታ ለፍጻሜው ያልፋሉ። በተጨማሪም ሁለት ፈጣን ሰዓት ያላቸው አትሌቶች ፍጻሜውን ይቀላቀላሉ።
ከሌሊቱ 6 ሰዓት ከ20 ላይ በወንዶች የ800 ሜትር የግማሽ ፍጻሜ ውድድር አትሌት ጀነራል ብርሃኑ ይወዳደራል።
አትሌት ጀነራል 1 ደቂቃ ከ45 ሴኮንድ ከ45 ማይክሮ ሴኮንድ የግል ምርጥ ሰዓቱ ነው።
በሶስት ምድብ በሚካሄደው ማጣሪያ ከየምድቡ አንደኛና ሁለተኛ የሚወጡ አትሌቶች በቀጥታ ለፍጻሜው ማለፋቸውን ያረጋግጣሉ።
በተጨማሪም ሁለት ፈጣን ሰዓት ያላቸው አትሌቶች ለፍጻሜው ውድድር ያልፋሉ።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው 1 የወርቅና ሁለት የብር በድምሩ 3 ሜዳሊያዎችን አግኝታ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ አውስትራሊያን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃ ይዛለች።