ቀጥታ፡

በባለልዩ ጣዕም ቡና ውድድር ዓለም አቀፍ ጨረታ የኢትዮጵያ አንድ ኪሎ ቡና በታሪክ ከፍተኛ በሚባል ገንዘብ ተሸጠ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2016 (ኢዜአ)፦ በአራተኛው የባለልዩ ጣዕም ቡና ውድድር (ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ) ዓለም አቀፍ ጨረታ የኢትዮጵያ አንድ ኪሎ ቡና ከ102 ሺህ ብር በላይ በመሸጥ አዲስ ክብረ ወሰን መመዘገቡን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

ውድድሩ ለአርሶ አደሮች ኑሮ መሻሻል አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) መንግስት የዜጎቹን ሕይወት ለመለወጥና ኑሯቸውን ለማሻሻል በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በቡና ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች የልፋታቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የባለልዩ ጣዕም ቡና ውድድር ከተጀመረ አምስት ዓመት ማስቆጠሩን አስታውሰዋል።

አራተኛው የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ውድድር በተለያዩ የውድድር መርሃ ግብሮች ላለፉት ሰባት ወራት ሲካሄድ መቆየቱን አመልክተዋል።

በዘንድሮው የውድድሩ ዓለም አቀፍ የኦንላይን ጨረታ ሂደት ተወዳዳሪ ለሆኑት ቡናዎች 4 ሺህ 870 የተለያዩ ዋጋ መሰጠቱንና ለአንድ ኪሎ ቡና የቀረበው የጨረታ ዋጋ ታሪካዊ ሆኖ መመዝገቡን ጠቁመዋል።


 

አንድ ኪሎ ቡና በ980 ነጥብ 64 ዶላር (በ445 ፓውንድ ) በኢትዮጵያ ከ102 ሺህ ብር በላይ በሆነ ዋጋ መሸጥ መቻሉን ገልጸዋል።

ይህም ዋጋ በኢትዮጵያ እስከ አሁን ከተካሄዱት ውድድሮች ሆነ በሌሎች መመዘኛዎች እጅግ ከፍተኛና አዲስ ክብረ ወሰን ሆኖ መመዘግቡን ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት።

ለአርሶ አደሮቹ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ትልቅ ድል በመሆኑ ሁሉንም ዜጋ በተለይም አርሶ አደሮችን እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት እወዳለሁ ብለዋል።

ውድድሩን ወደዚህ አገር ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት ላደረጉ ተቋማት፣ አርሶ አደሮች፣ በቡናው ዘርፍ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላትና አጋሮች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

አምስተኛው የባለልዩ ጣዕም ቡና ውድድር (ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ) በ2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

በውድድሩ ላይ ብዙ የቡና አርሶ አደር ተፎካካሪዎች በማቅረብ ብዙ ሚሊየነር አርሶ አደሮችን እንደምናፈራና ተመልሰን እንደምንገናኝ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ መግለጻቸውን ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም