ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ሳዑዲ አረቢያ የኢኮኖሚ ትስስራቸውን ማጠናከር የሚያስችላቸውን የንግድ ምክር ቤት አቋቋሙ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ሳዑዲ አረቢያ የሁለትዮሽ የኢኮኖሚ ትብብራቸውን ማጠናከር የሚያስችላቸውን አዲስ የንግድ ምክር ቤት አቋቁመዋል።

ምክር ቤቱ ሁለቱ አገራት ግብርና፣ ማዕድን፣ቱሪዝም፣ቤቶች፣ የምግብ ኢንዱስትሪ ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያላችውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰራ የሳዑዲ አረቢያው ዕለታዊ የእንግሊኛ ጋዜጣ አረብ ኒውስ በድረ ገጹ አስፍሯል።

በስምምነቱ ላይ የኢትዮጵያና ሳዑዲ አረቢያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የአገራቱ የግሉ ዘርፍ ተወካዮችና የሳዑዲ አረቢያ የንግድ ምክር ቤቶች ፌዴሬሽን አባላት የሆኑ ከ250 በላይ ባለሀብቶች ተገኝተዋል።

ምክር ቤቱ ከእ.አ.አ 2024 እስከ 2028 የሚቆይ መሆኑ ተጠቁሟል።

የምክር ቤቱ መቋቋም ሳዑዲ አረቢያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትብብር የማስፋት ስትራቴጂ አካል መሆኑ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ አገራት መካከል አንዷ መሆኗን ዘገባው አመልክቷል።

ኢትዮጵያና ሳዑዲ አረቢያ ካላቸው የኢኮኖሚ አምቅ አቅም አኳያ ያላቸውን የንግድ ልውውጥ መጠን ለማሳደግ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ከጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል።

የምክር ቤቱ መቋቋም የኢትዮጵያና ሳዑዲ አረቢያ የኢኮኖሚ እድሎች በመጠቀም ያላቸውን ትብብር ከማጠናከር፣ የንግድ ግንኙነቱን ከማሳለጥና የተቀናጀ የኢኮኖሚ ትስስር አኳያ ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ተጠቅሷል።

የንግድ ምክር ቤቱ መመስረት ይፋ የሆነው ከሶስት ወር ገደማ በፊት በአዲስ አበባ በተካሄደው የኢትዮ-ሳዑዲ አረቢያ የንግድ ፎረም መሆኑን የአረብ ኒውስ ዘገባ ያመለክታል።

ኢትዮጵያና ሳዑዲ አረቢያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1949 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ዋንኛ የንግድ አጋር ከሆኑ አገራት መካከል የምትጠቀስ ናት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም