የንግድ ሣምንት ኤግዚብሽኑ በጥራት ማምረትና ጥራትን ጠብቆ ለውጭ ገበያ ማቅረብን የሚያበረታታ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የንግድ ሣምንት ኤግዚብሽኑ በጥራት ማምረትና ጥራትን ጠብቆ ለውጭ ገበያ ማቅረብን የሚያበረታታ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2016(ኢዜአ)፦ የንግድ ሣምንት ኤግዚብሽኑ በጥራት ማምረትና ጥራትን ጠብቆ ለውጭ ገበያ ማቅረብን የሚያበረታታ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያዘጋጀው የንግድ ሣምንት ኤግዚብሽንና የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ማሳያ ማዕከልን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም ኤግዚብሽኑ በወጪ ንግድ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ንግድ ዘርፍ እየተከናወነ ያለውን ሥራ ተመልክተናል ብለዋል።
በንግድ ሣምንት ኤግዚብሽኑ በጥራት ማምረትና ጥራትን ጠብቆ ለውጭ ገበያ ማቅረብን ለማበረታታት የላቀ ሚና እንዳለው የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።
የምርት ጥራትን የማረጋገጡ ሥራ የተሰጠው ትኩረት የታየበት መሆኑን ጠቅሰው መሰል ስራዎች የወጪ ንግድን ለማሳደግ የሚያግዙ መሆኑንም አንስተዋል።
አምራቾች እንዲበረታቱ፤ ሸማቾች ጥራት ያለው ምርት እንዲያገኙ ማድረግ ተገቢ መሆኑን አንስተው በምርት ፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ ይገባልም ብለዋል።
የወጪ ንግድ እንዲሻሻል የሚያስችሉ አሰራሮችን መዘርጋትም ለነገ የማይባል ስራ መሆኑን ጠቅሰው ከተማ አስተዳደሩ በሁሉም ረገድ አብሮ የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ኤግዚቢሽኑ ከነሐሴ 19/2016 ጀምሮ በመካሄድ ላይ ሲሆን በነገው ዕለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።
በንግድ ሣምንቱ ከኤግዚብሽኑ ጎን ለጎን የፓናል ውይይትን ጨምሮ የተለያዩ መርኃ ግብሮች መካሄዱም ተገልጿል።