ቀጥታ፡

በምርት ጥራትና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከሀገርም ባለፈ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን ይገባል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2016(ኢዜአ)፦ በሁሉም ዘርፎች በምርት ጥራትና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከሀገርም ባለፈ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚገባ ተገለጸ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር "የኢትዮጵያን ይግዙ'' በሚል መሪ ኃሳብ ያዘጋጀው የንግድ ሣምንት እንደቀጠለ ሲሆን በዛሬው እለትም  የጥራት መሰረተ ልማት ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።  


 

በፓናል ውይይቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው፤ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ተወዳዳሪ ሆኖ የዘለቀው አየር መንገዱ የደንበኞቹን ፍላጎት በማሟላትና ለደህንነታቸው ቅድሚያ ሰጥቶ በመስራቱ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኛ ንጉስ መሆኑን በፅኑ በማመንና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአቪዬሽን አሰራርን ተከትሎ የሚሰራ በመሆኑ በስኬት መንገድ ላይ እየተጓዘ ያለ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል። 

በዚህ ረገድ አጠቃላይ የአየር መንገዱ የሰራተኞች የሙያ ስነ ምግባርን የተከተለ አገልገሎት፣ ከልብ የመነጨ ትጋትና ጥረት ታክሎበት የተገኘ ስኬት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በሁሉም ዘርፎች ጥራቱን የጠበቀ ምርትና አገልግሎት መስጠት የሀገር ኩራትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደረግ መሆኑን ተናግረዋል።

በሁሉም ዘርፎች በምርት ጥራትና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከሀገርም ባለፈ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን ይገባል ነው ያሉት።

ሌላኛው የአውደ ጥናቱ ተሳታፊ ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው፤ ከዓለም ጋር ለመወዳደር ጥራትና ምርታማነትን ማሳደግ የግድ ስለመሆኑ አንስተዋል።


 

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በምርትና ምርታማነት እንዲሁም በጥራት ጥሩ መነቃቃት የታየ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ የምርት ጥራትን ማእከል ያደረጉ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን የገበያ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የምርት ጥራትን ለማስጠበቅ እየተደረገ ባለው ጥረት በ5 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ግንባታው እየተጠናቀቀ ያለው የጥራት መሰረተ ልማት በቅርቡ ስራ የሚጀምር መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን ምርቶች የመግዛትና የመጠቀም ባህል እያደገና እየተለመደ መምጣት እንዳለበት አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም