ቀጥታ፡

ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች አምራች ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰው ሀይል እንዲያፈሩ ትኩረት ተሰጥቷል

ባህርዳር /ጎንደር /ደብረብርሀን//ሆሳእና፤ ነሐሴ 22/2016(ኢዜአ)፦ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች አምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚፈልገውን ብቁና የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራት እንዲችሉ ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ።

''ብቃት ለቴክኒክና ሙያ ልህቀት'' በሚል መሪ ሃሳብ ለቴክኒክና ሙያ የዘርፉ አካላት የተዘጋጀ ስልጠና በጎንደር፣ደብረብርሀን፣ ባህርዳርና ሆሳእና ከተሞች ዛሬ ተጀምሯል፡፡

በተለይም በጎንደር ከተማ በተጀመረው ስልጠና ላይ የተገኙት በፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት የቴክኒክና ሙያ ፋኩልቲ ዲንና የስልጠናው አስተባባሪ አቶ ታምራት ፍቃደ በወቅቱ እንደገለጹት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በእውቀትና ክህሎት የዳበረ ስራ ፈጣሪ ዜጋ በማፍራት የጎላ ሚና እየተወጡ ነው፡፡

ኮሌጆቹ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ብቁና የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራት እንዲችሉ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

በጎንደር ማዕከል በሚሰጠው ስልጠና ከተለያዩ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የተውጣጡ ከአንድ ሺ 600 በላይ ሰልጣኞች ተሳታፊ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ በበኩላቸው ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት መፋጠን ቁልፍ ሚና ከሚጫወቱ ውስጥ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

መንግስት አዲስ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ቀርጾ ተግባራዊ በማድረግ አምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ሀገራችን ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር የሰለጠነና ብቁ የሰው ሃይል በማፍራት የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የማይተካ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

ሰልጣኞች በቆይታቸው በሚቀስሙት እውቀትና ክህሎት በመታገዝ የተጀመረው የልማትና የእድገት ጎዳና እንዲሳካ አበክረው እንዲሰሩም አሳስበዋል፡፡


 

በአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አንዳርጋቸው ጎፋ በበኩላቸው እንደገለጹት ስልጠናው ዘርፉ ያመጣቸውን አዳዲስ እሳቤዎች መሰረት በማድረግ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳለጥ ምቹ መደላድል የሚፈጥር ነው።

በክልሉ በአራት የስልጠና ማዕከላት 5ሺ 973 ሰልጣኞች እየተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

''የአቅም ግንባታ ስልጠናው በዘርፉ አዳዲስ እሳቤዎች ዙሪያ ሰልጣኞች ተቀራራቢ ክህሎትና ግንዛቤ አንዲኖራቸው የማድረግ አላማ ያለው ነው'' ያሉት ደግሞ የጎንደር ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ዲን አቶ ተስፋሁን መኮንን ናቸው፡፡

አምራች ኢንዱስትሪው በመካከለኛ ደረጃ የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት ኮሌጁ ላለፉት ዓመታት ሙያተኞችን አሰልጥኖ ሲያቀርብ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በስልጠው ጎንደር ከተማን ጨምሮ ከሰሜን፣ ከደቡብ፣ ከማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የተውጣጡ የቴክኒክና ሙያ አሰልጣኞችና ዲኖች እየተሳተፉ ነው፡፡

በተመሳሳይ ስልጠናው በደብረብርሀን፣ በባህርዳርና በሆሳእና ከተሞች ዛሬ ተጀምሯል ።

በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተክለየስ በለጠ በወቅቱ እንደገለፁት እያደገ የመጣውን አምራች ኢንዱስትሪ ብቃት ባለው የሰለጠ የሰው ሃይል ማገዝ ያስፈልጋል።

ለዚህም በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በእውቀትና ክህሎት የዳበረ የሰው ሀይል ማፍራት ወቅቱ የሚጠይቀው አጀንዳ እንደሆነም ገልፀዋል።

መንግስት ዘርፉን በተሻለ ደረጃ በማዘመን በየአካባቢው እየተገነቡ ያሉ ኢንዱስትሪዎች የሰለጠነ የሰው ሃይል አቅርቦት እጥረት እንዳይገጥማቸው እየተደረገ ነው ብለዋል።

የደብረ ብርሀን ፖሊ ቴክኒክ ኮለጅ ዲን አቶ ባሻየ በየነ በበኩላቸው፤ ስልጠናው አዳዲስ እውቀቶችንና ክህሎቶችን በማስጨበጥ ተወዳዳሪ የሰው ሀይል ለማፍራት ያስችላል ብለዋል።

በዚህም በደብረ ብርሀን ከተማና አካባቢዋ እያደገ ለመጣው የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ዘርፍ በጥራትና በብቃት የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማፍራት እንደሚያግዝ አመልክተዋል።

በአማራ ክልል እውቀታቸውን በተግባር የሚያሳዩ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ምሩቃንን ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አማረ ዓለሙ ናቸው ።

የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ኢንዱስትሪዎች የሚፈልጉትን የሰው ሃይል በማፍራት የጎላ ሚና እየተወጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ለኢንዱስትሪዎች የበቃ የሰው ሃይል በብዛት ከማፍራት ባለፈም እውቀቱንና ክህሎቱን ተጠቅሞ በራሱ አቅም ስራ ፈጥሮ የሚንቀሳቀስ ትውልድ እየተገነባ ነው ብለዋል።

የተዘጋጀው ስልጠናም የአቅም ክፍተቶችን ከመሙላት ባለፈ አዳዲስና ወቅቱን የዋጁ ተጨማሪ እውቀትና ክህሎት ለመፍጠር የሚያግዝ እንደሆነ አብራርተዋል።

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ጉዳዮች ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር አቶ ገደፋው ሽፈራው በበኩላቸው እንዳሉት ስልጠናውን በስኬት ለማከናወን በትብብር እየተሰራ ነው።

ዩኒቨርሲቲው ለሰልጣኞች የምግብ፣ የመኝታ፣ የህክምናና ሌሎች አገልግሎቶችን ማመቻቸቱን ጠቅሰው “ይህን የሚከታተል ኮሚቴ ተዋቅሮ እየሰራ ነው” ብለዋል።

ከነሐሴ 22 እስከ ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ በሚሰጠው ስልጠና ሁለት ሺህ 100 የሚሆኑ የቴክኒክና ሙያ አሰልጣኞችና ዲኖች እየተሳተፉ ይገኛል።

በተመሳሳይ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ በተጀመረው ስልጠና ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቴክኒክና ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር ሰለሞን ፈርሻ በበኩላቸው የቴክኒክና ትምህርትና ስልጠና ተቋማት በእውቀትና ክህሎት የበቁ ስራ ፈጣሪ ዜጎችን ማፍራት የተሰጣቸው ሀገራዊ ተልዕኮ ነው ብለዋል።

የተጀመረውን ሁለንተናዊ የልማትና የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ በእውቀትና በክህሎት የበለፀገ የሰው ኃይል መፍጠር ከተቋማቱ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

ለዚህም ስኬት የቴክኒክና ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ከፍተኛ ሃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመው በተለይም ዜጎችን በክህሎት የማበልጸግ ስራን ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም