በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የውሃ ፓምፖች ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ለውሃ አቅርቦትና ግብርና ስራ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው - ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ - ኢዜአ አማርኛ
በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የውሃ ፓምፖች ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ለውሃ አቅርቦትና ግብርና ስራ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው - ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የውሃ ፓምፖች ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች በውሃ አቅርቦትና ግብርና ስራ ውስጥ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኝ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ።
የዓለም አቀፍ የሶላር አሊያንስ የፀሐይ ኃይል ልማትን አስመልክቶ ያዘጋጀው ስድስተኛው የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ ስብስባ በኮትዲቭዋር እየተካሄደ ይገኛል።
በውይይቱ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) በኢትዮጵያ በፀሐይ ኃይል ልማት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችና አፈጻጸምን አስመልክቶ ለመድረኩ ገለጻ አድርገዋል።
በዓለም አቀፍ የሶላር አሊያንስ ድጋፍ በኢትዮጵያ እየተተገበሩ የሚገኙ ስራዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በይርጋጨፌ ወረዳ ተገንብቶ የተጠናቀቀው የሶላር ፓምፕ ፕሮጀክት በአፍሪካ ደረጃ በተሞክሮነት ከተጠቀሱ ፕሮጀክቶች መካከል እንደሚገኝ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የውሃ ፓምፖች ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ለንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እንዲሁም ውሃን ለግብርና ስራ ለማዋል ቁልፍ አቅም እየሆኑ መምጣታቸውን አመልክተዋል።
ሚኒስትሩ ከውይይቱ ጎን ለጎን ከዓለም አቀፍ የሶላር አሊያንስ ዋና ዳሬክተር ዶክተር አጃይ ማቱር ጋር የተቋማቱን የትብብር ስራዎች ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በበይነ መረብ ውይይት አድርገዋል።
ዓለም አቀፉ የሶላር አሊያንስ አራተኛው ቀጣናዊ የኮሚቴ ስብሰባ በ2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ መካሄዱን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።