ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ተሳትፎዋ እስካሁን ስንት ሜዳሊያዎችን አግኝታለች?

20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ትናንት በፔሩ ሊማ ተጀምሯል።

በውድድር መክፈቻ ቀን አትሌት መዲና ኢሳ በ5000 ሜትር ሴቶች ፍጻሜ 14 ደቂቃ ከ39 ሴኮንድ ከ71 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ በመውጣት ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች።

አትሌት መቅደስ አለምእሸት ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ባለቤት ሆናለች።

በ5000 ሜትር ወንዶች ፍጻሜ አትሌት አብዲሳ ፈይሳ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።

ኢትዮጵያ በአንድ የወርቅና ሁለት የብር በድምሩ ሶስት ሜዳሊያዎች የሜዳሊያ ሰንጠረዡን እየመራች ነው።

በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመምና የሜዳ ተግባራትን ያካተተና እድሜቸው ከ20 ዓመት በታች የሆኑ አትሌቶች የሚሳተፉበት ውድድር ነው።

ውድድሩ ከእ.አ.አ. ከ1986 ጀምሮ የዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሚል ስያሜ ሲካሄድ ቆይቶ እ.አ.አ 2015  የስያሜ ለውጥ በማድረግ የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሚል እየተደረገ ይገኛል።

ኢትዮጵያ የዘንድሮውን ጨምሮ በሁሉም የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮናዎች ላይ ተሳትፋለች።

እ.አ.አ በ1986 በግሪክ አቴንስ በተካሄደው የመጀመሪያ ውድድር ኢትዮጵያ 1 የወርቅና 3 የነሐስ ሜዳሊያ በማግኘት ከ142 ተሳታፊ አገራት 14ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በ20 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ወንዶች ውድድር አትሌት ታደሰ ገብሬ አንደኛ በመውጣት ኢትዮጵያ በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ እንድታገኝ አስችሏል።

በዚሁ ውድድር አትሌት ነጋሽ ዱቤ ሶስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ አግኝቷል።

በተጨማሪም አትሌት መለሰ ፈይሳ በ5000 ሜትር ወንዶች እና አትሌት ደበበ ደምሴ በ10000 ሜትር ወንዶች በተመሳሳይ የነሐስ ሜዳሊያ አስገኝተዋል። ኢትዮጵያ በወቅቱ በውድድሩ ሜዳሊያ ያገኘች የአፍሪካ ብቸኛ አገር ነች።

እ.አ.አ በ1992 በኮሪያ ሪፐብሊክ ሴኡል በተካሄደው አራተኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በ5000 እና 10000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማግኘት አዲስ ታሪክ ሰርቷል።

ኢትዮጵያ በሴቶች በሻምፒዮናው ለመጀመሪያ ጊዜ ሜዳሊያ ያገኘችው እ.አ.አ በ1994 በፖርቹጋል ሊዝበን በተካሄደው አምስተኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ነበር።

በ800 ሜትር ሴቶች አትሌት ቁጥሬ ዱለቻ ሶስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች።

አትሌት ቁጥሬ እ.አ.አ በ1996 በአውስትራሊያ ሲድኒ በተካሄደው ስድስተኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና በ1500 ሜትር ሴቶች አንደኛ በመውጣት በውድድሩ ታሪክ ለኢትዮጵያ ወርቅ ያመጣች የመጀሪያ ሴት አትሌት መሆን ችላለች።

በ5000 ሜትር ሴቶች ፍጻሜም አትሌት አየለች ወርቁ የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ አስገኝታለች።

አትሌት አሰፋ መዝገቡ፣ አትሌት አበበች ንጉሴ፣ አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም፣ አትሌት መሰረት ደፋር፣ አትሌት መሰለች መልካሙ፣ አትሌት ኢብራሂም ጄይላን፣ አትሌት ታሪኩ በቀለ፣ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ፣ አትሌት ሙክታር እድሪስ፣ አትሌት ቡዜ ድሪባ፣ አትሌት ድርቤ ወልተጂ፣ አትሌት ሰለሞን ባረጋና አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ በሓምፒዮናው ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ካገኙ አትሌቶች መካከል ይገኙበታል።

በኮሎምቢያ ካሊ ከሁለት ዓመት በፊት በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 በታች ሻምፒዮና 6 የወርቅ ፣ 5 የብር እና 1 ነሐስ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎች በማግኘት አሜሪካና ጃማይካ ተከትላ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ ስኬታማ መሆን ችላለች።

በተለይም ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ማጠናቀቂያ ቀን ብቻ አራት ወርቅ እና ሁለት የብር ሜዳሊያዎችን በማግኘት ድንቅ ምሽት አሳልፋለች።

የኮሎምቢያው ውድድር ኢትዮጵያ በውድድሩ ተሳትፎዋ ታሪክ በርካታ ሜዳሊያዎችን የሰበሰበችበትና ከፍተኛ ደረጃን ያገኘችበት ነው።

ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው የእስካሁን ተሳትፎዋ የዘንድሮውን ጨምሮ 46 የወርቅ፣ 51 የብርና 32 የነሐስ በአጠቃላይ 129 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።

ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው የአጠቃላይ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ከአሜሪካና ኬንያ በመቀጠል ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

በፔሩ ሊማ እየተካሄደ የሚገኘው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።

ኢትዮጵያ በምትሳተፍባቸው ውድድሮች ተጨማሪ ሜዳሊያዎችን ታገኛለች ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም