ኮሚሽኑ የሀገር ሰላምና አንድነት እንዲጸና የጀመረው የምክክር ሂደት እንዲሳካ የሚጠበቅብንን እንወጣለን -የአገራዊ ምክክር ሂደት ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ የሀገር ሰላምና አንድነት እንዲጸና የጀመረው የምክክር ሂደት እንዲሳካ የሚጠበቅብንን እንወጣለን -የአገራዊ ምክክር ሂደት ተሳታፊዎች
ሀዋሳ፤ ነሃሴ 23/2016 (ኢዜአ)፦የምክክር ኮሚሽኑ የሀገር ዘላቂ ሰላምና አንድነት እንዲጸና የጀመረው የምክክር ሂደት የተሳካ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት እየተሳተፉ የሚገኙ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና አካል ጉዳተኞች ገለጹ ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሲዳማ ክልል አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ማካሄድ መጀመሩ ይታወሳል።
በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች፣ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የተቋማት ተወካዮች፣ የመንግስት አካላት ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እየተሳተፉ ነው።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና አካል ጉዳተኞች ተወካዮች እንዳሉት ኮሚሽኑ የሀገር ሰላምና አንድነት እንዲጸና የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያግዙ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲዳማ ሀገረ ስብከት የካህናት አስተዳደር ክፍል ኃላፊ መልአከ አርያም ቀሲስ አስረስ መላኩ እንደተናገሩት ኮሚሽኑ የሀገር ሰላምና አንድነት እንዲጸና የጀመረው ስራ እንዲሳካ ተሰሚነታቸውን ተጠቅመው የበኩላቸውን ይወጣሉ።
የኃይማኖት ተቋማት ሁልጊዜም ሰላምን የመስበክ ሃለፊነት እንዳለባቸው አስታውሰው ለምክክሩ ስኬታማነት ማህበረሰቡ የምክክሩ ባለቤት መሆኑን ተረድቶ የበኩሉን እንዲወጣ የሚያስችል ግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል የኡላማ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ ኡመር ቡሹራ በበኩላቸው የምክክር ሂደቱ ህዝቡ ተስፋ ያደረገበትና ለሃገር ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና ምሰሶ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ስለ ሰላምና ለስ ምክክር አስፈላጊነት ከማስተማር ባለፈ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ነጻና የሁሉም ተሳትፎ የተካተተበት በመሆኑ ከተወካዮች መረጣ ጀምሮ ደስተኛ ሆነው እየተሳተፉ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ከሲዳማ ክልል ቦርቻ ወረዳ የመጡት የሃገር ሽማግሌ አቶ ተስፋየ ደነቀ ናቸው።
በሚኖሩበት አካባቢ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሽምግልና የመፍታት ልምድ እንዳላቸው ገልጸው በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱም ለሀገር የሚጠቅሙ ጉዳዮች እንዲነሱ በማድረግ ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል አይነስውራን ማህበር ሰብሳቢ አቶ ኢዮብ ሌንዳሞ፣ በሀገራዊ ምክክሩ አካል ጉዳተኞች መሳተፋቸው የሂደቱን አካታችነት የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመሆኑም በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ አንድነትና ሰላም የሚያጸኑ ጉዳዮችን በማንሳት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ጠቅሰው አካል ጉደተኞችም የተገኘውን እድል ተጠቅመው በምክክር ሂደቱ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
ዛሬ በተጀመረው አጀንዳ ማሰባሰብ የተሳተፉ ከ1 ሺህ 800 በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችና ባለድርሻ አካላት በቡድን ተከፋፍለው በአንጀንዳዎቻቸው ላይ እየተወያዩ ይገኛሉ።
የሲዳማ ክልል አቀፉ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ለሰባት ቀናት እንደምቆይ ተመላክቷል።