የዕደ ጥበብ ሀብቶችን ወደ ኢኮኖሚ ምንጭነት መለወጥ የሚያስችል ድጋፍ ይደረጋል - የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የዕደ ጥበብ ሀብቶችን ወደ ኢኮኖሚ ምንጭነት መለወጥ የሚያስችል ድጋፍ ይደረጋል - የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር
አዳማ፤ ነሐሴ 22/2016(ኢዜአ)፦ የዕደ ጥበብ ሀብቶችን ወደ ኢኮኖሚ ምንጭነት መለወጥ የሚያስችል ድጋፍ ለዘርፉ ሙያተኞች እንደሚያደርግ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ከተለያዩ ክልሎች፣ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የዕደ ጥበብ አምራች ማህበራት የተሳተፉበት የኢትዮጵያ ዕደ ጥበብ አምራቾች ማህበራት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ዛሬ በአዳማ ተካሂዷል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ በጠቅላላ ጉባዔው ላይ እንደተናገሩት፤ ዘርፉን ይበልጥ ለማልማትና ከዘርፉ የሚገኘውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት ቅድሚያ የሚሰጠው ነው።
በተለይም የሙያው ባለቤቶች የዕደ ጥበብ ሀብቶችን ወደ ኢኮኖሚ ምንጭነት በመለወጥ የተሻለ ገቢ ማግኘት የሚያስችሉ ድጋፍ እንደሚደረግ አስረድተዋል።
ዘርፉ ከስራ ባለፈ የህዝባችንን ማንነትና የአኗኗር ዘይቤ ማሳያ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ ለሀገር ገጽታ ግንባታም ፋይዳው የጎላ እንደሆነም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዕደ ጥበብ አምራች ማህበራት ፕሬዝደንት ወይዘሮ እጅጋየሁ ኃይለጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ማህበሩ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ነው ብለዋል።
የዕደ ጥበብ ስራውን ከኋላ ቀር አሰራር ለማላቀቅ በሙያው የተሰማሩ ዜጎች ተጨማሪ እውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።
ከባህላዊ የማምረቻ ዕቃዎች ጎን ለጎን ስራቸውን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የዕደ ጥበብ ምርቱ ባህላዊ ይዘቱን ሳይለቅ በገበያ ተፈላጊ እንዲሆን ማህበሩ ድርሻውን እየተወጣ መሆኑንም አክለዋል።
አያይዘውም በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ የዕደ ጥበብ ውጤቶች የሚታዩበትን የገበያ ዐውደ ርዕይ በማዘጋጀት የዘርፉን ተወዳዳሪነት ለማሳደግም በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅሰዋል።
ከሐረሪ ክልል በጉባዔው ላይ የተሳፉት ወይዘሮ ሰአዳ አብዶሽ፣ በማህበር ተደራጅተው የክልሉን ህዝብ ባህልና ወግ የሚያንፀባርቁ አልባሳትና የቤት ማስዋቢያ ጌጣጌጦች እያመረቱ መሆኑን ተናግረዋል።
ማህበራቸው አምስት አባላት ያለው መሆኑንና ስራውን ከጀመሩ አራት ወራትን ማስቆጠራቸውን ገልጸው፤ በስራውም ህይወታቸውን እየደጎሙ፣ በአጭር ጊዜም ለውጥ ለማምጣት እየተጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ከገቢ ማስገኛነት በሻገር ባህልን ለማስተዋወቅ በክልሉ የቱሪስቶች መዳረሻዎች የመሸጫ ማዕከላት በማስፋፋት በኩል ድጋፍ እንደሚያስልጋቸው ጠቁመዋል።
ሌላዋ ከጋምቤላ ክልል በጉባዔው ላይ የተሳተፉት ወይዘሮ ኛሉክ ደንግ የክልሉን ባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጥ እያመረቱ ኑሯቸውን እየደጎሙ መሆኑን ይናገራሉ።
ከቆዳ፣ ከተለያዩ ጨሌዎችና ዶቃዎች የተዋበ የባህል አልባሳት በእጃችን ብቻ በመስራት ዘመናትን አስቆጥረናል ያሉት ወይዘሮ ኛሎክ ምርቱን በጥራትና በብዛት ለማምረት የሚያግዝ ቴክኖሎጂ ቢያገኙ የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስረድተዋል።
በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ዘርፉን በገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ በማለም የባህል አልባሳት መለያ ወይም ሎጎ ጸድቋል።
ከጉባዔው ጎን ለጎን ከክልሎች የመጡ ማህበራት ያመጧቸው ልዩ ልዩ የባህል አልባሳት የዕደ ጥበብ ውጤቶችም ለእይታ ቀርበዋል፡፡