ስልጠናው ሀገራዊ ተልዕኮ የያዘና በዘርፉ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ነው - የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ስልጠናው ሀገራዊ ተልዕኮ የያዘና በዘርፉ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ነው - የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር
መቀሌ/ሮቤ፤ ነሐሴ 22/2016(ኢዜአ)፦ ለቴክኒክና ሙያ አመራር አባላት እና አሰልጣኞች እየተሰጠ ያለው ስልጠና ሀገራዊ ተልዕኮ የያዘና በዘርፉ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።
"ብቃት ለቴክኒክና ሙያ ልህቀት" በሚል መሪ ሐሳብ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በሀገሪቱ ባሉ 17 ዩኒቨርሲቲዎች ለአሰልጣኝ መምህራን የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል።
ሚኒስቴሩ ከትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ፣ ትምህርትና ስልጠና እና ስራ እድል ፈጠራ ቢሮ እንዲሁም ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር "ብቃት ለቴክኒክና ሙያ ልህቀት" በሚል መሪ ሐሳብ በትግራይ ክልል ለሚገኙ የቴክኒክና ሙያ አመራር አባላት እና አሰልጣኞችም የአቅም ግንባታ ስልጠናውን እየሰጠ ነው።
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ዋና ግቢ እየተሰጠ ባለው ስልጠና ላይ የተገኙት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የተቋማት ማስፋፋትና አቅም ግንባታ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መብራቱ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ወጣቱ ስራ ፈጣሪ በመሆን ተወዳዳሪነቱ የሚጨምረው በቴክኒክና ሙያ ትምህርት እና ስልጠና ዘርፍ ነው።
ይህንን ከግምት በማስገባትም መንግስት የዘርፉን ስልጠና ጥራት የሚያሻሽሉ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሰጠ ያለው ስልጠናም ሰልጣኞች ተጨማሪ እውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ እንደሚያግዝ አመልክተው፤ ይህም ወደ ፊት ብቁ ተወዳዳሪ፣ ጥራት ያለው፣ ስራ ፈጣሪና አምራች ዜጋ ለመፍጠር እንዲተጉ ያደርጋል ብለዋል።
ስልጠናው የተቀናጀ እና ሀገራዊ ተልዕኮ የያዘ፣ እውቀትና ክህሎት የተላበሱ፣ በስራ እድል ፈጠራና ቴክኖሎጂ ማስፋፋት ላይ በቂ ግንዛቤ ያላቸው አሰልጣኞች እና ሰልጣኞች ለማፍራት ስለሚያግዝ መንግስት ልዩ ትኩረት እንደሰጠው አቶ መብራቱ ተናግረዋል።
ውጤት ተኮር የሆነ የስልጠና እና የተቋማት ግንባታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያመላከቱት።
በትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ፣ ትምህርትና ስልጠና እና የስራ እድል ፈጠራ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ገነት አረፈ በበኩላቸው፤ ሀገር አቀፉ ስልጠና በክልሉ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር እና ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን አመልክተዋል።
በመሆኑም ስልጠናው ለታሰበለት ግብ በተግባር እንዲውል የክትትልና ድጋፍ ሥራቸውን እንደሚያጠናክሩ ወይዘሮ ገነት ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ሥልጠናው በአጋርፋ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ እየተሰጠ ነው።
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአጋርፋ ኮሌጅ ማዕከል የሥልጠናው አስተባባሪ አቶ ጌታቸው ካፒቴ እንዳሉት፣ ሥልጠናው ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ መገንባት የሚያስችል የሰው ኃይል ለማፍራት ያለመ ነው።
እንዲሁም በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጆች እየተሰጠ የሚገኘውን የሥልጠና ጥራት ለማረጋገጥ አሰልጣኞች ላይ የሚደረገው ኢንቨስትመንት ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።
በአጋርፋ ኮሌጅ የሥልጠና ማዕከል በሁለቱ የባሌ ዞኖች የሚገኙ የፖሊ ቴክኒኮችና ከሦስት የግብርና ኮሌጆች የተውጣጡ አሰልጣኞችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኮሌጁ ዲን አቶ ፍራኦል ኢደኦ ናቸው።
ስልጠናው በቴክኒክና ሙያ፣ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ በተዘጋጁ ፖሊሲዎችና አዳዲስ እሳቤዎች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ መሆኑንም አመልክቷል።