ቀጥታ፡

ስልጠናው የቴክኒክና ሙያ ብቃትን ወደ ልህቀት ደረጃ በማሸጋገርና የተፈለገው ውጤት ለማምጣት ያግዛል

አርባ ምንጭ፤ነሐሴ 22/2016 (ኢዜአ)፦የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ያዘጋጀው ስልጠና የቴክኒክና ሙያ ብቃትን ወደ ልህቀት ደረጃ በማሸጋገር የተፈለገው ውጤት እንዲረጋገጥ መደላድል የሚፈጥር መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዮት ደምሰ ገለጹ።

"ብቃት ለቴክኒክና ሙያ ልህቀት" በሚል መሪ ሐሳብ በሥራና ክህሎት ሚኒስተር የተዘጋጀው የአሠልጣኝ መምህራን የአቅም ግንባታ ስልጠና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እየተሰጠ ነው።

በዚሁ ወቅት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዮት ደምሰ እንዳሉት "ዛሬ የተጀመረው ስልጠና የቴክኒክና ሙያ ብቃትን ወደ ልህቀት ደረጃ ለማሸጋገር ያግዛል" ብለዋል።

ይህ የአሠልጣኝ መምህራን የአቅም ግንባታ ስልጠና የቴክኒክና ሙያ ብቃትን ወደ ልህቀት ደረጃ ለማሸጋገር የሚሰሩ ስራዎችን ከማጠናከርና ውጤታማ ከማድረግ አንጻር ጉልህ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ ስልጠናው የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በአዳዲስ ፖሊሲዎችና የፖሊሲ እሳቤዎች በመታገዝ የሀገሪቷ ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ መደላድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በተለይም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የሚያሰለጥኗቸው የሰው ሃይል በፖሊሲዎች፣ በእሳቤዎችና በለውጥ አስተሳሰቦች ዘመኑን የሚመጥን ቴክኒካዊ ብቃት እንዲኖራቸው የሚያስችል ነው ብለዋል።

የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠናው የማይተካ ሚና ያለው በመሆኑ ማህበረሰቡ በዘርፉ ትክክለኛ ምልከታ እንዲጨብጥም ያግዛል ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት በክልሉ የሚገኙ የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ወደ አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲና እሳቤዎች ሙሉ ትግበራ መግባታቸውን ጠቅሰው፤ይህ ስልጠና የመምህራንን አቅም በማጎልበትና ትውልዱን በዕውቀትና ክህሎት ለማነጽ ወሳኝ ነው ብለዋል።

ለስልጠናው በዘርፉ በወጡ አዳዲስ ትምህርትና ስልጠና ፖሊሲዎችን ጨምሮ ስድስት የተለያዩ የሥልጠና ሰነዶች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተውውጣጡ 1 ሺህ 632 በላይ መምህራን በመሳተፍ ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በእያንዳንዱ ስልጠና አሠልጣኝ መምህራን ተገቢውን ዕውቀትና ክህሎት ይዘው እንድወጡ ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግም አቶ አብዮት ጠቁመዋል።

ከሠልጣኝ መምህራን መካከል በጎፋ ዞን የላሃ ከተማ ቴክኒክና ሙያ መምህር በረከት ሰጉ እንዳሉት ስልጠናው በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን የሚሞላ እንደሆነ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።

በተለይም በዘርፉ የወጡ አዳዲስ ፖሊሲዎችና እሳቤዎች በመታገዝ በክህሎት መር ዕውቀት የዳበረ ትውልድ ለመፍጠር ራስን ለማዘጋጀትና በዕውቀት ለመስራትም ያስችለናል ነው ያሉት።

ስልጠናው አገር አቀፋዊ በመሆኑ ችግሮችን ወጥነት ባለው መንገድ በመፍታት "ተቀራራቢና ተመሳሳይ ዕውቀትና ክህሎት እንድኖረን ያስችላል" ያሉት ደግሞ የአርባምንጭ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ መምህር ሞላልኝ በቀለ ናቸው።

በተጨማሪም ስልጠናው ልምድ ለመለዋወጥና ክህሎትን ለማዳበር ጠቃሚ መሆኑን አንስተው፤ "በአግባቡ በመከታተል ለቀጣይ ስራና ሃላፊነት አስፈላጊውን የዕውቀት ግብአት እሸምትበታለሁ ነው" ያሉት ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስተር ያዘጋጀው ይህ ስልጠና በመላው ሀገሪቷ በ17 ዩኒቨርሲቲዎች ከ23 ሺህ ለሚልቁ አሰልጣኝ መምህራን የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ሲሆን ለተከታታይ 12 ቀናት ቆይታ ይኖረዋል ነው የተባለው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም