የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የሕንድ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ የሚያደርጉት የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ምቹ መደላድል ይፈጥራል - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የሕንድ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ የሚያደርጉት የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ምቹ መደላድል ይፈጥራል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2016(ኢዜአ)፦ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የሕንድ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ የሚያደርጉት የኢንቨስትመንት ፍሰትን እንዲጨምር ዕድል ይፈጥራል ሲሉ በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ተናገሩ።
ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ መግባቷ ይታወቃል።
ማሻሻያው የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትንና ዘላቂነትን የሚደግፍ፣ ዘመናዊና ጤናማ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማዕቀፍ በመመሥረት ፈጠራን የሚያበረታታ፣ ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ ዘርፍ ከባቢ እንዲሁም ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ ነው።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር አኒል ኩማር፤ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የሚበረታቱ ናቸው።
እነዚህ ማሻሻያዎች የኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንት ምኅዳር ለማነቃቃት ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ይህም ሕንድን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ላሉ ኢንቨስተሮች ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን ያስችላታል ብለዋል።
በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአይ ሲ ቲ፣ በማዕድንና ቱሪዝም ዘርፍ የውጭ ባለኃብቶች ያላቸውን ተሳትፎ እንደሚያሳድግም ገልጸዋል።
አምባሳደሩ ማሻሻያው በብሪክስ አባል ሀገራት መካከል ትብብርና መደጋገፍን መሠረት ያደረገ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲኖር የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እያከናወነች ያለችው የሪፎርም ተግባራት ለብሪክስ አባል ሀገራት ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ጭምር ሁነኛ አጋር እንድትሆን ያደርጋታል ብለዋል።
ኢትዮጵያና ሕንድ በተለያዩ የትብብር መስኮች ላይ የተመሠረተ ጠንካራ አጋርነት ያላቸው ሀገራት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በሚቀጥሉት አራት ዓመታት በማክሮ ኢኮኖሚ የማሻሻያ እርምጃዎች ምክንያት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካይ በ8 በመቶ ያህል እንደሚያድግ፤ የዋጋ ንረት ወደ 10 በመቶ ዝቅ እንደሚል፤ የታክስ ገቢ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ 11 በመቶ እንደሚደርስ ይገመታል።
የመንግሥት ዕዳ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ወደ 35 በመቶ ዝቅ እንደሚል፤ የወጪና ገቢ ንግድ ዋጋ ወደ 20 ቢሊየን ዶላር እንደሚያድግ፤ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ 8 ቢሊየን ዶላር ከፍ እንደሚልና ዓለም አቀፍ የመጠባበቂያ ክምችት ከ10 ቢሊየን ዶላር በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል።