በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭቶችን በዘላቂነት የመፍታት ሂደት በተሳካ መልኩ ቀጥሏል- አቶ ብናልፍ አንዷለም - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭቶችን በዘላቂነት የመፍታት ሂደት በተሳካ መልኩ ቀጥሏል- አቶ ብናልፍ አንዷለም
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 22/2016(ኢዜአ)፦ በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭቶችን በዘላቂነት የመፍታት ሂደት በተሳካ መልኩ መቀጠሉን የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም ገለጹ።
በሐምሌ 2016 ዓ.ም የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አወል አርባ እና የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችን በውይይት በዘላቂነት ለመፍታት መስማማታቸው ይታወሳል።
በስምምነቱ መሠረትም የተፈናቀሉትን ወደ ቀያቸው የመመለስና ለግጭት መነሻ የሆኑ ጉዳዮችን በሕገ-መንግሥታዊና ሕጋዊ አሠራር መፍትሔ ለመስጠት ርዕሰ-መስተዳድሮቹ ቃል ገብተው ነበር።
በዚህም መሠረት የአፈጻጸሙን ሁኔታ በሰላም ሚኒስትሩ አስተባባሪነት ከፌዴራልና ከክልሎች የተውጣጣ ልዑክ በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች በመገኘት ገምግሟል።
የልዑካን ቡድኑ በቆይታው በአካባቢው የነበሩ ግጭቶችን ለማስቆም የተደረገውን ስምምነትና የቴክኒክ ኮሚቴውን የሥራ አፈጻጸም በጥልቀት አይቷል።
በመሆኑም አጠቃላይ ሂደቱንና የግምገማውን ውጤት አስመልክቶ የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በአፋርና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለማስቆም ከፌዴራልና ከሁለቱ ክልሎች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ተከታታይ ውይይቶች መደረጋቸውን አስታውሰዋል።
የሁለቱ ክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮችም ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ በደረሱት ስምምነት መሠረት ወደ ተግባራዊ የመፍትሔ እንቅስቃሴ መገባቱን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
በስምምነቱ መሠረትም በቅድሚያ ግጭትና ሰብዓዊ ጉዳትን ማስቆም እንዲሁም በግጭቱ ሳቢያ የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀያቸው መመለስ በሚል በሁለት ምዕራፍ የተከፈለ መሆኑን አስታውሰዋል።
በሁለቱም ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎችን ከታጠቁ ኃይሎች እንቅስቃሴ ነፃ በማድረግ የፌዴራል የፀጥታ ኃይል ማሰማራት አንዱ የስምምነቱ አካል መሆኑን አንስተዋል።
በእነዚህ የስምምነት ማዕቀፎች መሠረትም የአተገባበሩን ሁኔታ የሚገመግም አካል ወደ ሥፍራው መሰማራቱን ገልፀዋል።
ከፌዴራል ተቋማት፣ ከፀጥታ ኃይሎችና ከሁለቱም ክልሎች የተውጣጣ ልዑክ የስምምነቱን የመጀመሪያ ምዕራፍ አፈጻጸም መሬት ላይ ወርዶ ስለመገምገሙ አንስተዋል።
በግምገማው መሠረትም በአካባቢው መከላከያና ሌሎች የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች ተሰማርተው ግዴታቸውን በአግባቡ እየተወጡ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል።
የአካባቢው ሕዝብና የሁለቱም ክልሎች በየደረጃው ያሉ አመራሮች ለዘላቂ መፍትሔ በትጋትና በባለቤትነት እየሰሩ መሆኑንም በቀጥታ አረጋግጠናል ነው ያሉት።
በአካባቢው የነበሩ ግጭቶች መቆማቸው የአካባቢው ማኅበረሰብ በሰላምና በተረጋጋ ሁኔታ ህይወታቸውን መምራት መጀመራቸውን ጠቅሰው፤ ይኸው መልካም ጅምር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በግምገማው መሠረት የሰላም ሂደቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ በስኬት በመጠናቀቁ ወደ ምዕራፍ ሁለት ትግበራ ለመሸጋገር የሚያስችል ሁኔታ ላይ መሆኑን አንስተዋል።
በስምምነቱ ቀጣይ ምዕራፍም ግጭቶች በዘላቂነት በመፍታት ማኅበረሰብ አቀፍ ዕርቀ-ሰላም ማካሄድ እና ተፈናቃይ ወገኖችን በሙሉ ወደ ቀያቸው መመለስ መሆኑን ጠቁመዋል።
የጋራ መድረኮችን በማጠናከር የስምምነቱን አፈጻጸም በማጽናት በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች በፍፁም መተማመን አብሮነታቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የቴክኒክ ቡድኑን በማስተባበር ሲሰሩ የቆዩት በሚኒስትር ማዕረግ የሰላም ሚኒስትሩ አማካሪ ካይዳኪ ገዛኸኝ፤ በሁለቱ ክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮች ውል ስምምነት ማስፈጸሚያ ዝርዝር ዕቅዶች ገቢራዊ መደረጋቸውን ገልፀዋል።
የጠብ አጫሪነትን እንቅስቃሴ ማስወገድ፣ በነፃ ቀጣናው ገለልተኛ የፀጥታ ኃይል ማሰማራት፣ ሕዝባዊ ውይይትና ዕርቀ-ሰላም፣ ተፈናቃዮችን መመለስና ለግጭት መንስኤ የሆኑ የወሰን ጉዳዮችን ዘላቂ ዕልባት መስጠት የሚሉ መሆናቸውን አንስተዋል።
በዚህም በምዕራፍ አንድ የተከናወኑ ስኬቶችን ማስቀጠልንና ለቀጣይ ምዕራፍ ማስፈጸሚያ ዕቅዶች ወጥተው ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።
ይኸውም በሁለቱ ክልሎች አመራሮች፣ ጎሳ መሪዎች እና ሌሎች የኅብረተሰብ ተወካዮችን ያሳተፉ ውይይቶች በማድረግ ወደ ዕርቀ-ሰላም የማካሄድ ሥራዎች ይቀጥላሉ ብለዋል።
የመከላከያ ዘመቻ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል በላይ ስዩም፤ በስምምነቱ መሠረት ግጭቶችን በማስቆም በሂደት ለሰላማዊ መፍትሔ የሚበጁ መሠረቶች እየተቀመጡ መሆኑን አንስተዋል።
በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች በዘላቂነት ከችግር ለመውጣት በፍፁም ቅንነትና ዝግጁነት መንፈስ እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።
የፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፈንታ፤ በአካባቢው በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ግጭቶች ብዙ ጉዳቶችን ማስከተላቸውን አስታውሰው፤ አሁን ላይ የዘላቂ ሰላም ሂደቶች በጥሩ ሁኔታ መቀጠላቸውን ገልፀዋል።
በቀጣይም የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ-መስተዳድሮች በደረሱበት ስምምነት መሠረት ችግሩን በዘላቂን ለመፍታት የሚችሉ ቀጣይ ምዕራፎች የሚከናወኑ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት በየደረጃው ያለው አመራርና አጠቃላይ ማኅበረሰቡ በቀጣይነትም በትብብር እንዲሰሩ ኃላፊዎቹ አስገንዝበዋል።