በሶማሌ ክልል ሕዝብ ዘንድ ዋና ምግብ የሆነውን ሩዝ በራሳችን የማምረት ቁጭት ወደ ውጤት እየተቀየረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል ሕዝብ ዘንድ ዋና ምግብ የሆነውን ሩዝ በራሳችን የማምረት ቁጭት ወደ ውጤት እየተቀየረ ነው

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 22/2016(ኢዜአ)፦በሶማሌ ክልል ሕዝብ ዘንድ ዋና ምግብ የሆነውን ሩዝ በራሳችን የማምረት ቁጭት ወደ ውጤት እየተቀየረ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ሙሃመድ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ አሁን በመንግሥት የተጀመረው የመስኖ ሩዝ ልማት በዘላቂነት የተትረፈረፈ ምርት የሚያስገኝ እንዲሆን የባለኃብቶች ሰፊ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ሩዝ ከዓለማችን ስትራቴጂክ የምግብ ሰብሎች አንዱ ሲሆን፤ ግማሽ ያህሉ የዓለም ሕዝብ ደግሞ በዋና ምግብነት ይጠቀመዋል።
ኢትዮጵያም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በጀመረችው አገራዊ ኢኒሼቲቭ ትኩረት ከተሰጣቸው የምግብ ሰብሎች ሩዝ አንዱ ሲሆን ከዚህ ቀደም በተወሰኑ አካባቢዎች በዝናብ ላይ በተመሰረተ ልማት ይመረት ነበር።
ከዝናብ ባሻገር ሩዝን በመስኖ የማልማት ሀገራዊ ውጥን ከወራት በፊት በሶማሌ ክልል ሸበሌ ዞን ቤርአኖ ወረዳ መጀመሩ ይታወቃል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ሙሃመድ፤ በክልሉ እስከ 3 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ሩዝ የማልማት ሥራ መጀመሩን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት በሸበሌ ዞን የደረሰ የሩዝ ምርት መሰብሰብ መጀመሩን ጠቁመዋል።
ይህ የምሰኖ ሩዝ ልማት የሙከራ ስራ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ሰፊ ለም መሬትና ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች እያሉ ሰፊ ልማት አለመኖሩ አሁን ላይ ቁጭት ፈጥሯል ብለዋል።
በተለይም የሶማሌ ክልል አብዛኛው ሕዝብ ሩዝ ተመጋቢ ቢሆንም ከማምረት ይልቅ ከውጭ የሚገባ ሩዝ ነው ሲመገብ የኖረው ብለዋል።
አሁን የሩዝ ምርትን በክልል በመስኖ ለማምረት የተጀመረው የሙከራ እንቅስቃሴ በማኅብረሰቡ ዘንድ ያለንን የውሃና የመሬት ኃብት በመጠቀም ማልማት አለብን የሚል መነቃቃትን መፍጠሩንም አንስተዋል።
የሙከራ ሥራው ሲጀመር የነበሩ ክፍተቶችን ከፌደራል መንግሥት ጋር በመቀናጀት በመቅረፍ ግብዓት በማቅረብ ቁጭታችንን ወደ ውጤት የሚቀይር ሥራ ላይ ነን ብለዋል።
ይህንን በመንግሥት ኢኒሼቲቭ የተጀመረ የመስኖ ሩዝ ልማት በዘላቂነት የተትረፈረፈ ምርት የሚያስገኝ እንዲሆን ባለኃብቶች እየተሰማሩ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የክልሉ መንግሥትም የባለኃብቶች ተሳትፍ እንዲጨምር አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አንስተዋል።
የክልሉ የግብርና ቢሮ ኃላፊ አብዱልቃድር ኢማን (ዶ/ር) በበኩላቸው በክልሉ ከለውጡ በፊት በሰብል ይለማ የነበረው መሬት 400 ሺህ ሄክታር እንደነበር አውስተው አሁን ላይ ወደ 885 ሺህ ሄክታር ማደጉን ጠቁመዋል።
በምርት ረገድም ከለውጡ በፊት የነበረው 7 ሚሊዮን ኩንታል ዓመታዊ ምርት አሁን ላይ ወደ 26 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን ነው የጠቀሱት።
የክልሉ ሰላም መረጋገጥ የግብርና ልማትን ለማስፋፋት ጉልህ ሚና ተጫውቷል የሚሉት ኃላፊው ከዚህ ቀደም ወደ ልማት ያልገቡ እንደ ሩዝ ያሉ ሰብሎችን በመስኖ ማልማት መጀመሩንም ገልጸዋል።
ሩዝ የሶማሌ ክልል ባህላዊ ምግብ ነው ያሉት ዶክተር አብዱልቃድር ይህንን ምርት በዋናነት በራስ የማምረት ሥራ በውጤታማነት እየተተገበረ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የክልሉ ህዝብ አብዛኛው አርብቶ አደር በመሆኑ ወደ ሰብል ልማት ለማስገባት የአስተሳሰብ ለውጥ ለመፍጠር እስከ ቀበሌ ድረስ የህዝብ ንቅናቄ መፈጠሩን አንስተዋል።
በዚህም ማኅበረሰቡ ኃሳቡን በቁጭት እንደተቀበለው አንስተው፥ በርካታ ባለኃብቶችና አርብቶ አደሮች ወደ ልማቱ እየገቡ ነው ብለዋል።
የክልሉ የመስኖና ተፋሰስ ቢሮ ኃላፊ መሀመድ ፋታህ መሀመድ፤ የሶማሌ ክልል ቆላማና ዝናብ አጠር መሆኑን ታሳቢ ያደረገ የግብርና ልማት በመተግበር ላይ መሆኑን አብራርተዋል።
በክልሉ ከሚገኙ ጥቂት ወንዞች መካከል የሸበሌ ወንዝን በመጠቀም በቤርአኖ ወረዳ 1 ሺህ 710 ሄክታር መሬት ላይ ሩዝና ሌሎች ሰብሎች በመስኖ እየለሙ ነው ብለዋል።
በቂ ውሃና የመስኖ መሰረተ ልማት መኖሩን ጠቅሰው በመስኖ የግብርና ልማት ላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለኃብቶች እንዲሳተፉ የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
በክልሉ እየለማ በሚገኘው የመስኖ ሩዝ ልማት ከተሰማሩ አርሶ አደሮች መካከል ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በአሜሪካ በግብርና ስራ ሲተዳደሩ የነበሩት መሀሙድ ሸሪፍ አብዲ አንዱ ናቸው።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ያካበቱትን የግብርና ኢንቨስትመንት በሀገራቸው ለመተግበር የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ያነሳሉ።
የተሰማሩበት አካባቢ በቁጥቋጦ የተሸፈነ ለም አፈር እንደነበር አውስተው፥ በ25 ሄክታር ላይ ሩዝ እያለማን ነው ብለዋል።
የፌዴራልና የክልሉ መንግስት ድጋፍ በልማቱ ውጤታማ እንዲሆኑ እያገዛቸው መሆኑን ጠቅሰው፥ በቀጣይ እስከ 200 ሄክታር መሬት ለማልማት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ቀደም ሲል በክልሉ በነበረው የሰላም እጦት ሳቢያ ለስደት ተዳርገው የቆዩት አቶ አብዱልሃኪም እስማኤል ፥ ለውጡን ተከትሎ በተፈጠረው ሰላም ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው በቤርአኖ ወረዳ ከሌሎች አልሚዎች ጋር ሩዝን በመስኖ እያለሙ ናቸው።
አቶ አብዱልሃኪም በማኅበር ተደራጅተን ማልማት መጀመራችን አቅማችንን እንድናሰባስብና ከመንግሥት በቀላሉ ድጋፍ እንድናገኝ አስችሎናል ይላሉ።
መንግሥት የመስኖ መሰረተ ልማትን አሟልቶ እንዳቀረበላቸው ጠቅሰው ሙሉ የማዳበሪያ የምርጥ ዘርና ሌሎች ግብዓቶችንም ማግኘታቸውን አንስተዋል።
አሁን ኪሳራ የሌለው ትርፋማ ልማት ላይ ነን ያሉት አቶ አብዱልሃኪም በተለይም እርሳቸውን ጨምሮ የአካባቢው ማኅበረሰብ የሩዝና ሌሎች የእርሻ ሥራዎችን እንዴት በቅንጅት እንደሚተገበሩ ግንዛቤ አግኝተንበታል ብለዋል።