በምስራቅ ጎጃም ዞን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ጎጃም ዞን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው
ደብረ ማርቆስ፤ ነሐሴ 22/2016(ኢዜአ)፡-በምስራቅ ጎጃም ዞን በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ግማሽ ሚሊዮን ሰዎችን በማሳተፍ የበጎ ፈቃድ ስራው ተጠናክሮ እንደቀጠለ የዞኑ ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ገለፀ።
የመምሪያው ሃላፊ አቶ ቢሻው ሞላ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በተያዘው ክረምት ወጣቶችን እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማሳተፍ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ ነው።
በጎ ፈቃደኞቹ ባደረጉት ጥረትም በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ከመትከል ባለፈ አራት ሺህ 900 ሄክታር በላይ የአቅመ ደካሞችን መሬት በሰብል ዘር መሸፈንና የአረም ስራ ማከናወናቸውን ገልፀዋል።
እንዲሁም 97 የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤቶችን በአዲስ የመገንባትና 150 የሚሆኑ መኖሪያ ቤቶችን ደግሞ ተጠግነው ለተጠቃሚዎቹ ማስረከብ እንደቻሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በጥሬ ገንዘብ እና የአልባሳትም ድጋፍ ማድረጋቸውን እና 85 ዩኒት ደም መሰብሰብ መቻሉንም ተናግረዋል።
ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት መቻሉን ጠቅሰው፤ ቤተሰቦቻቸው አቅም ለሌላቸው ተማሪዎችም የመማሪያ ቁሳቁስ እና ዩኒፎርም በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኙም አስረድተዋል።
የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራው እስከ መስከረም አጋማሽ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስገንዝበዋል።
የአዋበል ወረዳ የከይት ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ጓዴነህ አንዷለም እንዳለው፤ ‘’የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት መቻሌ የህሊና እርካታ ሰቶኛል’’ ብሏል።
በዚህ ክረምትም በችግኝ ተከላ እና በአቅመ ደካማ ቤቶች ጥገና የተሳተፈ መሆኑን ጠቁሞ፤ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግሯል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሦስት ዓመታት እንደተሳተፈ ጠቅሶ፤ በመጪው የበጋ ወቅት በሚከናወነው የበጋ በጎ ፈቃድ ስራም እንደሚሳተፍ አስታውቋል።
የአነደድ ወረዳ የቀበሌ 02 ነዋሪ ወጣት ዘካሪያስ ይሁን በበኩሉ፤ በበጋም ሆነ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጿል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራዊ ግንኙነቱን ከማሳደጉም በላይ የስራና እርስ በእርስ የመረዳዳት ባህልን የበለጠ የተማረበት መሆኑን ተናግሯል።
በዚህ የክረምት ወቅት በጎ ፈቃደኞች በአገልግሎት ብዛት ያረጀ ቤታቸውን ጠግነው ተጠቃሚ እንዳደረጓቸው የገለፁት ደግሞ በአነደድ ወረዳ 02 ቀበሌ ነዋሪ እማሆይ አስረሳች ካሴ ናቸው።
በጎ ፈቃደኞች ባደረጉት ጥረት ከችግራቸው መላቀቃቸው እንዳስደሰታቸው ጠቅሰው፤ ለተደረገላቸው ድጋፍም አመስግነዋል።
በዞኑ ባለፈው ዓመት በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከተሰማሩ ከ580 ሺህ በላይ ወጣቶች ከመንግስት ይወጣ የነበረን ከ450 ሚሊየን ብር በላይ የሸፈነ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡