ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ሳይንሳዊ የወንጀል ምርመራና ትንተና ሂደትን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2016 (ኢዜአ)፦  የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ሳይንሳዊ የወንጀል ምርመራና ትንተና ሂደትን ይበልጥ በማዘመንና በማጎልበት የፍትሕ ሥርዓቱን ለማጠናከር በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ። 

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መስፍን አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት፤  ዩኒቨርሲቲው በአፍሪካ በፖሊስ ትምህርትና ሥልጠና የልህቀት ማዕከል ለመሆን የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

በተለያዩ የውጭ አገራት ሲሰጥ የነበረውን የፎረንሲክ ሥልጠና በአገር ውስጥ ለመጀመር የሚያስችሉ ሥራዎች መጀመራቸውን ገልጸው፤ ከዚህ አንጻር በዩኒቨርሲቲው እየተገነባ ያለውን የፎረንሲክ ኢንስቲትዩት ለአብነት አንስተዋል።

በቀጣይ ዓመት ኅዳር ወር የሚጠናቀቀው ይህ ኢንስቲትዩት ትምህርት ብቻ ሳይሆን ሥልጠናና ምርመራን በማቀናጀት ለፖሊስ አገልግሎት ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል። 

የኢንስቲትዩቱ ግንባታ እውን ሆኖ ሥራ ሲጀምርም የፎረንሲክ ምርመራን ጨምሮ የአሻራ፣ የሰነድ ምርመራና ሌሎችንም ዘመናዊ የወንጀል ምርመራ በመስጠት ለፍትሕ ሥርዓቱ መጠናከር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ የፎረንሲክ ምርመራ የሚሰሩ ባለሙያዎችን የማሰልጠን ሥራም እንደሚሰራም ነው ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መስፍን የገለጹት።

ኢንስቲትዩቱ ዓለም አቀፍ ምዘናን እንዲያሟላ ተደርጎ እንደሚደራጅ የገለፁት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ በተመራማሪዎችና በሳይንቲስቶች በመደገፍ ምርመራው፣ ጥናታዊ ምርምሩና ሥልጠናው በተቀናጀ መልኩ እንደሚከናወን አብራርተዋል።

በዘርፉ ካሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ያለውን ቅንጅታዊ አሠራር ለማጠናከር ከተለያዩ አገራት የፖሊስ ሥልጠና ማዕከላት ጋር በጋራ መሥራት የሚያስችል ሥምምነት እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የፖሊስና ሲቪል ስትራቴጂክ ተቋማት አመራር ጥናትና ምርምር የሚያከናውኑበት፣ ልምድ የሚያጋሩበት፣ሥልጠና የሚሰጡበት ተጨማሪ የፖሊስ አመራር የሥልጠና ማዕከል በግንባታ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የማዕከሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ በአመራር ዘርፍ የሚታዩ ክፍተቶችን በሥልጠናና ምርምር ለመፍታት እንደሚያግዝና፤ ከቀጣናዊ አልፎ በአህጉር ደረጃ ልምድ፣ እውቀትና ጥናቶች የሚከናወኑበት ማዕከል ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል።

                    

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም