17ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 22/2016 (ኢዜአ)፦በፓሪስ አስተናጋጅነት የሚካሄደው 17ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀመራል።

የፓራሊምኩ የመክፈቻ ስነ ስርዓት በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከስታዲየም ውጪ ይደረጋል።

በውድድሩ ላይ ከ184 አገራት የተወጣጡ 4 ሺህ 400 አትሌቶች በ22 የስፖርት ዓይነቶች ይወዳደራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ በውድድሩ በአትሌቲክስ ስፖርት በሁለቱም ጾታዎች በስድስት አትሌቶች ትወከላለች።

አትሌቶቹ በአገር ቤት የሁለት ወራት ዝግጅት ያደረጉ ሲሆን ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሽኝት እንደተደረገለት ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ለመሳተፍ ነሐሴ 19 ቀን 2016 ዓ.ም ወደ ፓሪስ አቅንቷል።

የኢትዮጵያ አትሌቶች በ1 ሺ 500 ሜትር በአራት የአካል ጉዳት ዘርፎች ይወዳደራሉ።

እ.አ.አ በ2021 በቶኪዮ በተካሄደው 16ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች በውድድሩ ታሪክ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣችው አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ በጭላንጭል(T-13 የውድድር ዓይነት) ትሳተፋለች።

አትሌት ያየሽ ጌቴ በአይነስውር (T-11 የውድድር ዘርፍ) ተወዳዳሪ ናት።

በወንዶች አትሌት ይታያል ስለሺ ይግዛው በበኩሉ በአይነስውር ጭላንጭል (T-11) ትወዳደራለች።

በእጅ ጉዳት (T-46 ምድብ) አትሌት ገመቹ አመኑ ኢትዮጵያን ወክሎ ይወዳደራል። በተጨማሪም አትሌቶቹን የሚደግፉ ሁለት አሯሯጭ አትሌቶች ይሳተፋሉ።

17ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የመክፈቻ ስነ ስርዓት በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከስታዲየም ውጪ ይደረጋል።

ስነ ስርዓቱ ‘ ፕሌስ ዴ ላ ኮንኮርድ’ በተሰኘው ታዋቂ የሕዝብ አደባባይና የ‘ሻምፕ ኢሊዜ’ ጎዳና ላይ ይከናወናል።

የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች በክረምት ወቅት ሲካሄድ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ውድድሩ ይካሄድ የነበረው በበጋ ወቅት ነበር።

ውድድሩ እስከ ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።

17ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የአካልና የስነ አዕምሮ ጉዳት ያለባቸው አትሌቶች የሚሳተፉበት ዓለም አቀፍ የባለ ብዝሃ ስፖርቶች ውድድር ነው።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2021 በቶኪዮ በተካሄደው 16ኛው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች በአንድ የወርቅ ሜዳሊያ ከዓለም 56ኛ ከአፍሪካ ስድስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።

የመጀመሪያው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የተካሄደው እ.አ.አ በ1960 በጣልያን ሮም ነበር። በታሪካዊው ውድድር ላይ 29 አገራት ተሳትፈዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም