ሀገራዊ ምክክሩ ለሀገራዊ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ይዞ የመጣ የታሪክ ምዕራፍ በመሆኑ ሁሉም ተሳትፎውን ማጠናከር አለበት... ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ለሀገራዊ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ይዞ የመጣ የታሪክ ምዕራፍ በመሆኑ ሁሉም ተሳትፎውን ማጠናከር አለበት... ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር
ሐዋሳ፤ነሐሴ 22/2016 (ኢዜአ)፡-ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ለሀገራዊ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ይዞ የመጣ የታሪክ ምዕራፍ በመሆኑ ሁሉም በሂደቱ የሚያደርገውን ተሳትፎ ማጠናከር እንዳለበት የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር አስገነዘቡ።
ኮሚሽኑ በሲዳማ ክልል አጀንዳ ለማሰባሰብ ያዘጋጀው መድረክ ዛሬ በሐዋሳ ከተማ ተጀምሯል።
በዚሁ ወቅት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር፣ ''ሀገራዊ የምክክር መድረክ ሊያመልጠን የማይገባ የታሪክ ምዕራፍ ነው'' ብለዋል።
በመሆኑም በሐሳብ ልዩነት ምክንያት የተፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭቶች ያስከተሉትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በመመካከር መፍታት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
እስካሁንም በተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተደረገው አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት የተሳካ እንደነበረ ገልጸዋል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የምታደርገው ሀገራዊ የምክክር መድረክ መሆኑን ገልጸው፤ በሂደቱ ለሚሳተፉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
''በሀገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የመመካከር ልምድና ባህል ቢኖርም የአሁኑ በሀገር ጉዳይ ሁሉም በአንድ ላይ የምንወያየው መድረክ ነው'' ብለዋል።
''ባለመስማማታችን ምክንያት ተፈጥሯዊ ጸጋዎቻችንና ሀብቶቻችንን በሚፈለገው ልክ እንዳንጠቀም እንቅፋት ሆኖብናል'' ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የመላው ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ የሆነው የምክክር ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
''የምክክር መድረኩ ምዕራፍ አንዳችን ስለአንዳችን የምናወራበት ሳይሆን መላው ኢትዮጵያዊያን በመከባበርና በእኩልነት ስለ ሀገራቸው የሚመክሩበት ነው'' ያሉት ደግሞ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ ናቸው።
''ከዘመናት የመናገር ፖለቲካ ወጥተን የምንመካከርበትና የምንደማመጥበት እድል መጠቀም ይገባል'' ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ''አንድነታችንን አስጠብቀን የጋራ ግንዛቤ ይዘን ጠንካራ ማህበረሰብና ሀገር የምንገነባበት ምዕራፍ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ ከክልሉ 45 ወረዳዎች የተወከሉ 1 ሺህ 800 የማህበረሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የተለያዩ ተቋማት ተወካዮች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተወካዮችና ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እየተሳተፉ ነው።
እነዚሁ በምክክር መድረኩ የሚሳተፉ አካላት ከህዝብ የተሰጣቸውን ውክልና በሀቀኝነት ለመወጣት በመድረኩ ላይ ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።