ቀጥታ፡

በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ 200 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች መሳብ ተችሏል - የኢንዱስትሪ ሚኒስትር

ሀዋሳ ፤ ነሐሴ 22/2016(ኢዜአ) ፦ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ  በ2016 በጀት ዓመት 200 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ካፒታል ያስመዘገቡ አዳዲስ ኢንቨስተሮችን መሳብ እንደተቻለ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ ።

ሚኒስቴሩ የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ የሚመክር ግምገማ በሀዋሳ አካሂዷል ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች ።


 

ይህን ለማጠናከር የተለያዩ ስትራቴጂዎች ተነድፈው በልዩ ትኩረት እየተሰሩ መሆኑን አንስተው፤ እነዚህ ተግባራት ውጤት እያመጡ መሆናቸውን አንስተዋል ።

በዚህም ባለፈው በጀት ዓመት በተደረገው እንቅስቃሴ ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 1 ሺህ 109 የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮችን መሳብ እንደተቻለ አቶ ታረቀኝ ገልጸዋል።

ይህም በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ''ያሉንን ዕድሎች በመጠቀም ከዚህ በላይ በማሳደግ በአገራዊ ዕድገት የበኩሉን እንዲወጣ ይሰራል'' ብለዋል ።

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በአገራዊ የዕድገት ድርሻ ላይ ከዚህ ቀደም ካለበት በእጅጉ እየላቀ የመጣ ቢሆንም፤ ከዚህ በላይ ለማሳደግ እንደሚሰራ ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል።

ለዚህም ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ለመሳብና የኢንዱስትሪ የማምረት አቅምን ለማሳደግ ይሰራል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ለዘርፉ ማነቆ የሚሆኑ የኃይል አቅርቦት፣ የግብዓት እጥረትና የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግሮችን ለማቃለል በትኩረት  እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ከኢንዱስትሪው ፍላጎት አኳያ ማሰልጠንና ማብቃት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ለዚህም የኢንዱስትሪ ባለቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ማዕከላት አትኩረው እንዲሰሩ ይደረጋል ብለዋል። 


 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ግዛው ጋጊያብ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የአምራች ኢንዱስትሪን ዘርፍ ለማጠናከር ባለድርሻ አካላትን በማቀናጀት ውጤት እየተገኘ ነው።

እንዲሁም የገበያ ትስስርን ለመፍጠር የሚያስችሉ የተለያዩ ባዛሮችና ሌሎች አማራጮች በማመቻቸት አቅማቸው እየጎለበተ መምጣቱን ነው የገለጹት።

ክልሉ ማርና እርድን ጨምሮ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ዕምቅ አቅም ያለው መሆኑን ያመለከቱት አቶ ግዛው፤ ወደ ክልሉ ኢንቨስትመንት ለመሳብ  በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ቀልጣፋ አሰራርና መሬትን ጨምሮ ሌሎች አቅርቦቶችን አመቻችቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ባለፈው በጀት ዓመት ከ16 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስመዘገቡ 141 ባለሀብቶችን  መሳብ እንደተቻለም ተናግረዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በክልሉ ኢኮኖሚ ላይ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲጫወት የኃይል አቅርቦትና መሠረተ ልማትን ጨምሮ ማነቆ እንዳይሆኑ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑም አመልክተዋል።


 

የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ኢድሪስ በበኩላቸው፤ በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኢንቨስትመንት ዘርፍ በተደረገው  እንቅስቃሴ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል።

በተለይም በክልሉ የአምራች ኢንዱስትሪን የማምረት አቅምን ለማጠናከር መሰረተ ልማት የማሟላት ስራዎች አሳታፊ በሆነ መልኩ መከናወናቸውን አንስተው፤ በዚህም አበረታች ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

በዚህም በርካታ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ስራ እንዲገቡ እንዲሁም እያመረቱ ያሉት ደግሞ ተወዳዳሪ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸውን ኃላፊው ጠቅሰዋል።

በክልሉ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ተኪ ምርት እንዲመረት ሰፊ ስራ ተሰርቶ ውጤት መገኘቱን ጠቁመዋል፤ ከኢንዱስትሪና ከሆርቲካልቸር  ምርቶች  800 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን አስታውቀዋል።

በክልሉ የኢንዱስትሪ የማምረት አቅም እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው፤ ''ካለን የመልማት አቅም አኳያ ብዙ ስለሚቀረን በ2017 በጀት ዓመት ታቅዶ ይሰራል'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም