ቀጥታ፡

በዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የማጣሪያ ውድድሮች ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 22/2016 (ኢዜአ)፦ በፔሩ ሊማ እየተካሄደ በሚገኘው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ሶስት የማጣሪያ ውድድሮች ይከናወናሉ።

ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ50 የወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል ማጣሪያ ይደረጋል። አትሌት ኃይሉ አያሌውና አትሌት በሪሁን ሞገስ ይወዳደራሉ።

በምድብ ሁለት የሚወዳደረው አትሌት ኃይሉ በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም በሃዋሳ በተካሄደው 12ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና 8 ደቂቃ ከ47 ደቂቃ ከ6 ማይክሮ ሴኮንድ ሶስተኛ በመውጣት የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓት ማስመዝገቡ ይታወቃል።

በምድብ 1 የሚገኘው አትሌት በሪሁን በተመሳሳይ በሃዋሳ በተካሄደው ውድድር 8 ደቂቃ ከ49 ሴኮንድ ከ1 ማይክሮ ሴኮንድ አራተኛ በመውጣት የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓት አስመዝግቧል።

በሁለት ምድብ በሚደረገው ማጣሪያ ከየምድቡ ከአንድ እስከ ስምንት የሚወጡ አትሌቶች ለፍጻሜ ያልፋሉ።

ከሌሊቱ 6 ሰዓት ከ10 የ1500 ሜትር ወንዶች ማጣሪያ ይደረጋል። በውድድሩ ላይ አትሌት አብዲሳ ፈይሳና አትሌት ሰንደል ሙሳ ይሳተፋሉ።

በምድብ 2 የሚወዳደረው አብዲሳ በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም በስፔን በተከናወነ ውድድር 3 ደቂቃ ከ32 ሴኮንድ ከ37 ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቱን አስመዝግቧል።

አትሌቱ ትናንት በሻምፒዮናው በ5000 ሜትር ወንዶች የብር ሜዳሊያ ማግኘቱ ይታወቃል።

በምድብ ሶስት የሚገኘው አትሌት ሰንደል ሙሳ በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም በሃዋሳ በተካሄደው 12ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና 3 ደቂቃ ከ39 ሴኮንድ ከ7 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቱን አስመዝግቧል።

ሰንደል ከሁለት ዓመት በፊት በታንዛንያ ዳሬሰላም በተካሄደው የአፍሪካ ታዳጊ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1500 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቱ የሚታወስ ነው።

በሶስት ምድብ ተከፍሎ በሚደረገው ማጣሪያ ከየምድባቸው ከአንድ እስከ አምስት የሚወጡ አትሌቶች ፍጻሜውን ይቀላቀላሉ።

ከሌሊቱ 6 ሰዓት ከ45 ላይ በሚካሄደው የሴቶች 1500 ሜትር ማጣሪያ አትሌት ፅጌ ተሾመና አትሌት ሳሮን በርሄ ይወዳደራሉ።

በምድብ 1 የምትገኘው አትሌት ፅጌ በሃዋሳ በተካሄደው 12ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና 4 ደቂቃ ከ9 ሴኮንድ ከ4 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቷን አስመዝግባለች።

በምድብ ሁለት የምትወዳደረው አትሌት ሳሮን በሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም በቻይና ሺያሜን በተካሄደ ውድድር 3 ደቂቃ ከ59 ሴኮንድ ከ21 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቷን አስመዝግባለች።

ሳሮን በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም በካሜሮን ዱዋላ በተካሄደው 23ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1500 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ ይታወሳል።

በሶስት ምድብ ተከፍሎ በሚደረገው የማጣሪያ ውድድር ከየምድባቸው ከአንድ እስከ አምስት የሚወጡ አትሌቶች ለፍጻሜ ያልፋሉ።

በተያያዘም ትናንት በሻምፒዮናው መክፈቻ ቀን በ5000 ሜትር ሴቶች ፍጻሜ አትሌት መዲና ኢሳ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች። አትሌት መቅደስ አለምእሸት ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ባለቤት ሆናለች።

በ5000 ሜትር ወንዶች የፍጻሜ አትሌት አብዲሳ ፈይሳ የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።

ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ንብረት ክንዴ ስድስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም