አትሌት መዲና ኢሳ በዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኘች - ኢዜአ አማርኛ
አትሌት መዲና ኢሳ በዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኘች
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2016(ኢዜአ) ፦ በ20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና በ5000 ሜትር ሴቶች የፍጻሜ ውድድር አትሌት መዲና ኢሳ አንደኛ በመውጣት ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች።
አትሌት አብዲሳ ፈይሳ በ5000 ሜትር ወንዶች የፍጻሜ ውድድር የብር ሜዳሊያ ለአገሩ አምጥቷል።
አትሌት መዲና 14 ደቂቃ ከ39 ሴኮንድ ከ71 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ በመውጣት ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች። መዲና በርቀቱ የሻምፒዮናውን ክብረ ወሰን አሻሽላለች።
አትሌቷ የመጨረሻውን የአንድ ኪሎ ሜትር ለብቻዋ በመሮጥ በአስደናቂ የአጨራረስ ብቃት አሸንፋለች።
መዲና ከሁለት ዓመት በፊት በኮሎምቢያ ካሊ በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና በ5000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ የሚታወስ ነው።
አትሌቷ በሁለት ተከታታይ ሻምፒዮናዎች በተመሳሳይ ርቀት የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት አዲስ ታሪክ ሰርታለች።
ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት መቅደስ አለምእሸት 14 ደቂቃ ከ57 ሴኮንድ ከ ማይክሮ ከ44 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።
ዩጋንዳዊቷ አትሌት ቻሪቲ ቼሮፕ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች።
በሻምፒዮናው የመጀመሪያው ሜዳሊያ የሚያስገኘው ውድድር በኢትዮጵያ አሸናፊነት ተጠናቋል።
በተያያዘም በ5000 ሜትር ወንዶች የፍጻሜ ውድድር አትሌት አብዲሳ ፈይሳ 13 ደቂቃ ከ41 ሴኮንድ ከ56 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ አስገኝቷል።
ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ንብረት ክንዴ ስድስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
ኬንያዊው አትሌት አንድሪው ኪፕሩቶ አላሚሲ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል።
ዩጋንዳዊው ኬኔት ኪፕሮፕ የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት ሆኗል።
በ20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት ሻምፒዮና የመጀመሪያ ቀን ውሎ ኢትዮጵያ አንድ የወርቅና ሁለት የብር ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።