አዘርባጃን በሰው ሰራሽ አስተውሎት(ኤአይ) ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራት እንደምትፈልግ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
አዘርባጃን በሰው ሰራሽ አስተውሎት(ኤአይ) ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራት እንደምትፈልግ ተገለጸ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2016(ኢዜአ)፦ አዘርባጃን በሰው ሰራሽ አስተውሎት(ኤአይ) ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራት እንደምትፈልግ ገለጸች።
በአዘርባጃን ፕሬዚደንት ጽህፈት ቤት የዓለም አቀፍ ጉዳይ ዳይሬክተር ጀነራል መሀመድአሊ ኩዳቨርዴቭ የተመራ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ልዑክ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የስራ ጉብኝት አድርጓል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) የልዑክ ቡድኑን በመቀበል የኢንስቲትዩቱን የስራ እንቅስቃሴ እና እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ ገለጻና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የአዘርባጃን ልዑክ መሪ መሀመድአሊ ኩዳቨርዴቭ አዘርባጃን በዘርፉ ፈጠራ መር መፍትሄዎችን በማፍለቅ በውጤታማነት መተግበሯን በተመለከተ ልምድ አጋርተዋል።
አዘርባጃን በሰው ሰራሽ አስተውሎት(ኤአይ) ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራትና በመላ አፍሪካ ያላትን ትብብር ማሳደግ እንደምትፈልግም የልዑክ መሪው ገልጸዋል።
ጉብኝቱ ሁለቱ ሀገራት በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ ያላቸውን ተሞክሮ የተለዋወጡበትና በቀጣይ በትብብር ሊሰሩባቸው የሚችሉባቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች መለየት ላይ ያተኮረ እንደነበር ከኢንስቲትዩቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) ተቋማቸው በተለይም በሰው ሰራሽ አስተውሎት(ኤአይ) እና በሌሎች እየለሙ ባሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ላይ ከአዘርባጃን ጋር በቅርበትና በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳለው መናገራቸውም ተገልጿል።