ቀጥታ፡

ዓለም አቀፍ የገበያ ዕድሎችን አሟጦ ለመጠቀም ለምርቶች ጥራት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2016(ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፍ የገበያ ዕድሎችን አሟጦ ለመጠቀምና የወጪ ንግዱን አስተማማኝ መሰረት ለማስያዝ ለምርቶች ጥራት ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተመላከተ። 

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተዘጋጀውና ''የኢትዮጵያን ይግዙ'' የንግድ ሳምንት መካሄዱን ቀጥሏል። 

የንግድ ሣምንቱ አካል የሆነውና በወጪ ንግዱ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።

በውይይቱ በተለይም በኢትዮጵያ የወጪ ንግዱ ማነቆዎችና መፍትሄዎቻቸው ላይ ያተኮሩ ኃሳቦች ተነስተዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ውጪ የምትልካቸው ምርቶች በብዛትና በጥራት አለመመረት፣ ኮንትሮባንድ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የገበያ መዳረሻ አለመስፋትና የዓለም አቀፍ ገበያ መዋዠቅ ከወጪ ንግድ የሚፈለገውን ያህል ገቢ እንዳይገኝ እንቅፋት ሆነው መቆየታቸው ተጠቅሷል።


 

በፓናል ውይይቱ የመነሻ ኃሳብ ካቀረቡት መካከል የኢትዮጵያ ሰነደ መዓለ ንዋዮች ገበያ ዋና ዳይሬክተር ጥላሁን ካሳሁን(ዶ/ር) ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እያካሄደችው ያለው ድርድር አንዱ ዓላማ ሕጋዊ መሰረት ያላቸው ዓለምአቀፍ የገበያ ዕድሎች ለመጠቀም ነው ብለዋል።

አገራት ነጻ የገበያ ዕድሎችን በፈለጉት ጊዜ ማንሳትና መስጠት የሚችሉ መሆኑን ገልጸው፣ አገሪቷ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ከሆነች የገበያ ዕድሉን በቀላሉ ማግኘት ያስችላታል ብለዋል።

ዓለምአቀፍ ሥምምነቶችን መሰረት አድርገው የሚገኙ ዕድሎችን አሟጦ ለመጠቀም ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ጥራት ላይ አበክሮ መሥራት ተገቢ መሆኑንም ነው ያነሱት።

የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶች የተቀባዮችን ፍላጎት ማሟላት እንዲችሉ ከምርት ሂደት ጀምሮ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግባቸው ይገባል ብለዋል።

በተለይም ለምርት ለጥራት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ አንስተው የወጪ ንግዱን ሊያሳልጡ የሚያችሉ መሰረተ ልማቶችም ይበልጥ ሊጠናከሩ ይገባል ነው ያሉት።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በበኩላቸው የዓለምን ገበያ ታሳቢ በማድረግ ምርቶችን ጥራታቸውን በመጠበቅ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ማምረት ተገቢ ነው ብለዋል።


 

ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በብዛትም ሆነ በስብጥር የማምረት አቅም ቢኖራትም አቅሟን አሟጦ መጠቀም ላይ ብዙ መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ አሁን ላይ ምርትና ምርታማነቱ እያደገ ቢመጣም የተመረተውን ምርጥ አሟጦ ለገበያ ማቅረብ ላይ ውስንነቶች መኖራቸውንም ነው ሚኒስትሩ ያነሱት።

በኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ፈተና ሆኖ የቆየውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት የወጪ ንግዱ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩንም ጠቅሰው በዚህ ምክንያት ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶች ለኮንትሮባንድ እንዲጋለጡ በማድረግ አገሪቷ ከዘርፉ ማግኘት የነበረባትን ጥቅም አሳጥቷል ብለዋል።

በቅርቡ የተደረገው የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያ የወጪ ንግዱን ከኮንትሮባንድ ለመታደግ መፍትሄ መሆኑን አንስተዋል። 

የወጪ ምርቶችን በጥራትና በብዛት በማምረት ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ጉዳዮችን ለይቶ መፍትሔ እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም