የኢትዮጵያን ፖሊስ ተቋማት የመፈጸም አቅም ለማሳደግ የሚሰጡ ስልጠናዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ፖሊስ ተቋማት የመፈጸም አቅም ለማሳደግ የሚሰጡ ስልጠናዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን ፖሊስ ተቋማት የመፈጸም አቅም ለማሳደግ የሚሰጡ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
በሴኩሪቲ ሎው ኤንድ ኢንፎርስመንት ስልጠና ቻይና አገር ለሚጓዙ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣የክልል ፖሊስና ለሪፐብሊካን ጋርድ ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ ሽኝት ተደርጎላቸዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከቻይና ሕዝብ ደህንነት ሚኒስቴር ጋር ባለው ጠንካራ ትብብር አማካኝነት የተለያዩ የስልጠና ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም በቻይና በተሰጡ አምስት ዙር ሥልጠናዎች የኢትዮጵያ ፖሊስ አመራርና አባላት ከፍተኛ ልምድና ተሞክሮ ማግኘታቸውን አስታውሰዋል።
ተቋሙ አዳዲስ የስልጠና ክፍሎችን በማቋቋም የኢትዮጵያ ፖሊስን የውስጥ አቅም ከመገንባት ባሻገር ለአፍሪካ አገራት በዘርፉ ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያን የፖሊስ ተቋማት የመፈጸም አቅም ለማሳደግ በአገር ውስጥና በውጪ አገራት የሚሰጡ ስልጠናዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ማለታቸውን ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ከፍተኛ አመራሮች የሥልጠና ቆይታቸው ልምድና ተሞክሮ የሚቀስሙበት እንዲሁም የላቀ ውጤት የሚያስመዘግቡበት እንዲሆን ኮሚሽነር ጀነራሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።