የታጠቁ ኃይሎች ሰላማዊ መንገድ በመምረጥ በአገራዊ ምክክሩ ላይ እንዲሳተፉ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል - የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
የታጠቁ ኃይሎች ሰላማዊ መንገድ በመምረጥ በአገራዊ ምክክሩ ላይ እንዲሳተፉ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል - የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን
ሀዋሳ ፤ ነሐሴ 21/2016 (ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ትጥቅ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ሰላማዊ መንገድን በመምረጥ በምክክር ሂደቱ እንዲሳተፉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ነገ በሲዳማ ክልል የሚጀመረውን አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር መሀሙድ ድሪር ትጥቅ ያነሱ ወገኖች በምክክር ሂደቱ በመሳተፍና በመመካከር ጥያቄዎቻቸውን እንዲያነሱ ተደጋጋሚ ጥሪ ከማቅረብ ባሻገር ለሂደቱ ስኬት ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
በዚህም ከለላ በመስጠት፣ ሰላማዊ መንገድ መከተልና የአደራዳሪዎችን ተሳትፎ በማካተት ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በአገራዊ እውቀትና ባህል መሰረት ግጭቶች የሚፈቱባቸው መንገዶች በመኖራቸው አማራጩን ተጠቅሞ በምክክር ሂደቱ መሳተፍ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸው፤ መገናኛ ብዙሃንም ግንዛቤውን በማስጨበጥ ረገድ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።
ከምክክር ውጪ ያለው አማራጭ አገርን የሚያፈርስ፣ ኢኮኖሚን የሚጎዳና ውድ የሆነውን የሰው ሕይወት የሚቀጥፍ በመሆኑ የተሻለውን መንገድ መከተል ውጤታማ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ትጥቅ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ሰላማዊ መንገድ በመምረጥ ወደ ምክክር ሂደቱ እንዲመጡ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በበኩላቸው የምክክር ኮሚሽኑ የተቋቋመው በአገራዊ መግባባት ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍና ለግጭት መንስኤ ለሆኑ ጉዳዮች የጋራ መፍትሄ ለማበጀት መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ የተለያዩ ጥያቄዎች አሉን ብለው ትጥቅ ያነሱ ወገኖችን ጥያቄም መመለስ የሚያስችል ስልጣን አለው ያሉት ኮሚሽነሩ የኮሚሽኑን ጥሪ ተቀብለው በምክክር ሂደቱ ሊሳተፉ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ጥሪውን ተቀብሎ ለሚመጡ አካላት ኮሚሽኑ ሕጉን ተከትሎ አስፈላጊውን ሁሉ የሚያመቻች መሆኑን ጠቁመው፤ አሁንም እድሉን ሊጠቀሙ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የኮሚሽኑ አሳታፊነት ትጥቅ ያነሱ ወገኖችን ጭምር የሚያካትት ነው ያሉት ደግሞ ኮሚሽነር ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ ናቸው።
በአገሪቷ ጉዳይ ሁሉም ዜጎች የመሳተፍ እድል እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
የምክክር ሂደቱ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ያሉ ዜጎች አጀንዳዎቻቸውን በግጭት ሳይሆን በምክክር በመነጋገር እንዲፈቱ የሚያስችል መድረክ ነው ብለዋል፡፡
ትጥቅ ያነገቡ ወገኖች ለአገር የሚጠቅም አጀንዳ ይኖራቸዋል ብለን ስለምናሰብ ተሳትፏቸው ይፈለጋል ሲሉ ተናግረዋል።
መገናኛ ብዙሃን ተሳትፏቸው የሚኖረውን ፋይዳ በማስገንዘብ በኩል ሚናቸውን እንዲወጡና ለምክክሩ ውጤታማነት እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡
በሲዳማ ክልል ነገ በሚጀመረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ ከ1ሺህ 800 በላይ ዜጎች የሚሳተፉ ሲሆን፤ የማህበረሰብ ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንደሚሳተፉ ተመልክቷል፡፡