ቀጥታ፡

የመንገድ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ በጥናትና ምርምር ላይ ያተኮረ ሥራ መሥራት ይገባል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የመንገድ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ በማጠናቀቅ የኃብት ብክነትን ለማስቀረት በጥናትና ምርምር ላይ ያተኮሩ ሥራዎች መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ።

ሰባተኛው ዓመታዊ የመንገድ ጥናት ጉባዔ "በጥናትና ቴክኖሎጂ ልህቀት ዘላቂና ውጤታማ የመንገድ ትስስርን እውን እናድርግ!" በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ ጉባዔ በአዲስ አበባ ተካሄደ።

የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ መንግሥት ለመንገድ ልማት በየዓመቱ በቢሊየን የሚቆጠር በጀት ይመድባል።

ከፍተኛ ገንዘብ የሚወጣባቸውን የመንገድ ፕሮጀክቶች በጥራት፣ በተያዘለት ጊዜና በጀት በማጠናቀቅ የሕዝብን ተጠቃሚነትና እርካታ ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅት በተያዘላቸው ጊዜ የሚጠናቀቁ ፕሮጀክቶች 32 በመቶ ብቻ በመሆናቸው በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል።

ለዚህም የዲዛይን፣ የአስተዳደርና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ጥራቱን በጠበቀ መንገድ በመገንባት ረዥም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ችግሮችን በጥናት ላይ ተመስርቶ መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል።

ክፍተቶችን በማሳየትና ቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመሥራት ዓመታዊ የመንገድ ጥናት ጉባዔው አቅጣጫ የሚያሳይ እንደሆነ ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የመንገድ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ወርቁ አስራቴ (ዶ/ር) ማዕከሉ ለመንገድ ልማት ዘርፍ አጋዥ የሆኑ ጥናትና ምርምሮችን እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

የፕሮጀክት ማኔጅመንት ብቃት፣ ውጤታማነት፣ ጥራት፣ በተያዘለት ጊዜና በጀት ከማጠናቀቅና ተያያዥነት ያላቸው ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጥናቶች እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር አስቴር ዮሐንስ በበኩላቸው፤ በመንገድ ዘርፍ የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮችን ለመንገድ ልማትና አስተዳደር ውጤታማነት ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።


 

በመንገድ ግንባታ ከቁሳቁስ አጠቃቀም፣ ከጥራትና ሌሎች ጉዳዮች ጋር የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ላቦራቶሪ በማቋቋም ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በመንገድ ምርምር ጉባዔው የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የዘርፉ ተመራማሪዎች የተገኙ ሲሆን፤ በመንገድ ልማት ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥናትና ምርምሮች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ዘላቂነት ያለው የመንገድ ልማትና የመንገድ ኃብት አስተዳደርን በምርምር ከመደገፍ አንጻር ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸው ተነስቷል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም