ቀጥታ፡

ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የኤሌክተሪክ ተደራሽነትን ለማስፋፋት የሚሰራው ስራ ውጤት እያመጣ ነው -- የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

አዳማ፤ነሐሴ 21/2016 (ኢዜአ)፡-ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የኤሌክተሪክ ተደራሽነትን ለማስፋፋት የሚሰራው ስራ ውጤት እያመጣ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

እ.ኤ.አ ከ2021 እስከ 2026 እየተተገበረ የሚገኘው 'የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ብርሃን ተደራሽነት ፕሮጀክት' የአፈፃፀም ግምገማ ባለድሻ አካላት በተገኙበት በአዳማ እየተካሄደ ነው።

የፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ በጀት ከኢትዮጵያ መንግስትና ከዓለም ባንክ የተገኘ 270 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መሆኑም ተገልጿል።

በዚሁ ወቅት በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር አማካሪ አቶ ሞቱማ መቃሳ እንደገለፁት በፕሮጀክቱ በርካታ ዜጎችን የኤሌክትሪክ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

እ.ኤ.አ ከ2018 እስከ 2023 ዓ.ም በቆየው ብሔራዊ የኤሌክትሪክፊኬሽን ትግበራ ፕሮግራምም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን የማረጋገጥ ስራ መከናወኑን አስታውሰው፤ በፕሮግራሙም ከ10 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ብርሃን ተደራሽነት ፕሮጀክትም በሶላር ቴክኖሎጂ አማካኝነት የአገሪቷን የገጠር  ህብረተሰብ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ አክለዋል።

በዚህም በሶላር ሚኒ ግሪድ 240 ሺህ ቤተሰቦች የፀሐይ ሃይል ተጠቃሚ የሚሆኑ ሲሆን እስካሁን 85 የገጠር አካባቢዎች ላይ ውል ተገብቶ የሶላር ቴክኖሎጂ የገጠማ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም 1 ሺህ 400 ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማት በፀሐይ ሃይል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸው፤ በፕሮጀክቱ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ 10 የአገሪቷ ዋና ዋና ከተሞች የኤሌክትሪክ አቅርቦትን አስተማማኝ ለማድረግ መታቀዱንም አስረድተዋል።

ፕሮጀክቱ ሁለተኛውን የመካከለኛ ዘመን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት ግብ ከማሳካት አኳያም የጎላ ሚና ያለው መሆኑንም አመልክተዋል።

በአጠቃላይ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር እየተከናወነ የሚገኘው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነት የማስፋፋት ስራው ውጤት እያመጣ መሆኑን ጠቁመዋል።

''የትግበራ ጊዜው እስከ 2026 የሚዘልቀው የብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራምም ከ10 ሚሊዮን በላይ ተጨማሪ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው'' ያሉት ደግሞ በሚኒስቴሩ የኤሌክትሪፊኬሽንና ኢነርጂ መረጃ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ዳቢ ናቸው።


 

ከዋናው የኤሌክትሪክ ሃይል ቋት ርቀው የሚገኙ የገጠር ነዋሪዎችና ተቋማትን በሶላር ቴክኖሎጂ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ በማድረግ በኩል ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አክለዋል።

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ብርሃን ተደራሽነት ፕሮጀክትም ከብሔራዊ ሃይል ቋት ውጭ ያሉ በገጠር አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች፣ የንግድና ማህበራዊ ተቋማት  የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።

በተለይም የግል ኩባንያዎች በሶላር ቴክኖሎጂ ግንባታ ስራ ላይ እንዲሳተፉ የማበረታታት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም