ተጨማሪ የቻይና ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና ኢንቨስት እንዲያደርጉ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ተጨማሪ የቻይና ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና ኢንቨስት እንዲያደርጉ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2016(ኢዜአ)፦ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና በሚገኙ የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ተጨማሪ ቻይናውያን ባለሃብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን በቻይና የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈራ ደርበው ገለጹ፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሰሃ ይታገሱ(ዶ/ር) በቻይና የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተፈራ ደርበው እና የኢኮኖሚ ዘርፍ ምክትል አምባሳደር ደዋኖ ከድር ጋር በበይነ መረብ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ተጨማሪ የቻይና አምራች ኩባንያዎችና ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና በፋርማሲዩቲካል፣ በቴክስታይልና ጋርመንት እንዲሁም በአግሮ ፕሮሰሲንግ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ምክክር ማድረጋቸው ተመላክቷል።
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያለውን ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ ለማስተዋወቅ ሊሰሩ በሚገባቸው ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ሀሳብ መለዋወጣቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃ ያመለክታል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) በውይይቱ ወቅት በ13ቱም ኢንዱስትሪ ፓርኮችና በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና ያሉ አዳዲስ የኢንቨስትመንት አማራጮችንና እድሎችን ማብራራታቸውም ተጠቅሷል።
እድሉን በመጠቀምም ተጨማሪ ቻይናውያን ባለሃብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውንና ለዚህም ከኤምባሲው ጋር በጋራ እንደሚሰሩ አክለዋል።
በተጨማሪም ለአመታት ግንባታው የተጓተተውን የአዳማ ሁናን ኢንቨስትመንት ማዕከል ማስጀመር እና በቀጣይ በእቅድ ተይዘው በጋራ መከናወን በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መግባባት ላይ መደረሱም ተገልጿል።
በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያሉ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮችንና ማበረታቻዎችን በስፋት የማስተዋወቅ አቅም ያላቸው የቻይና ባለሃብቶችን የማወያየትና ኢንቨስት እንዲያደርጉ የማግባባት ተግባር በቀጣይ ከፍተኛ ትኩረት የሚሠጥባቸው ጉዳዮች መሆናቸው ተመላክቷል።
ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮችና የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና የቻይናውያን ባለሀብቶች ተሳትፎ በግምባር ቀደምትነት የሚነሳ መሆኑ ይታወቃል።