ሰባተኛው ዓመታዊ የመንገድ ጥናት ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሰባተኛው ዓመታዊ የመንገድ ጥናት ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ሰባተኛውን ዓመታዊ የመንገድ ጥናት ጉባዔ በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል።
ውይይቱ እየተከናወነ የሚገኘው "በጥናትና ቴክኖሎጂ ልህቀት ዘላቂና ውጤታማ የመንገድ ትስስርን እውን እናድርግ! " በሚል መሪ ሀሳብ ነው።
በጉባዔው ላይ የዘርፉ ተመራማሪዎች፣የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የግንባታ ዘርፍ አማካሪዎች፣ ኮንትራክተሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።
የከተማና መሠረተ-ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የግንባታው ዘርፍ ለመንገድና ቤቶች ልማት አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት (ጂዲፒ)፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለዘላቂ ምጣኔ ሀብት እድገት ያለውን ድርሻ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
በመንገድ ግንባታ የተለያዩ የአገሪቱን ክፍል እርስ በእርስ በማስተሳሰር የንግድና የሰዎችን እንቅስቃሴ ማሳለጥ እንደተቻለም ጠቅሰዋል።
መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት የመንገድ ሽፋንና ተደራሽነት እያደገ መምጣቱን ነው ሚኒስትር ዴኤታው የገለጹት።
የዘርፉ ቁልፍ ጉዳዮች በሆኑት ጥራት፣ደህንነትና የአካባቢ ተስማሚነት ላይ በትኩረት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ጉባዔው ጥናትና ምርምር፣ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂን በመጠቀምና ቅንጅታዊ አሰራርን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሒሩት ዮሐንስ በበኩላቸው፤ የመንገድ ግንባታ ጥራት፣ የፕሮጀክት አስተዳደር፣ አፈጻጸምን ለማሻሻል ጥናትና ምርምሮችን በመተግበር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸፐዋል።
በጉባዔው ላይ በመንገድ ልማት ላይ ያተኮሩ ጥናቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተጠቁሟል።