የሕዳሴ ግድብ ተጨማሪ ሁለት ተርባይኖች ወደ ሥራ መግባት ኢትዮጵያ ቀጣናውን በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር የምታደርገው ጥረት አመላካች ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴ ግድብ ተጨማሪ ሁለት ተርባይኖች ወደ ሥራ መግባት ኢትዮጵያ ቀጣናውን በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር የምታደርገው ጥረት አመላካች ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2016(ኢዜአ)፦የሕዳሴ ግድብ ተጨማሪ ሁለት ተርባይኖች ወደ ሥራ መግባት ኢትዮጵያ ቀጣናውን በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር የምታደርገው ጥረት አመላካች ነው ሲሉ የቀድሞ የግድቡ ተደራዳሪና የውኃ ኃብት ተመራማሪው ፈቅ አሕመድ ነጋሽ ገለጹ።
የሕዳሴ ግድብ ሁለት ተጨማሪ ተርባይኖች ሥራ መጀመራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት የወንዝ ፍሰት ሳይስተጓጎል ከመቀጠሉም በተጨማሪ የግድቡ የውኃ ማስተንፈሻ በሮች ተከፍተው ተጨማሪ 2 ሺህ 800 ሜትር ኪዩብ ውኃ በሰከንድ ማፍሰስ ጀምረዋል ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውኃ ፍሰትን በመቆጣጠር፣ የጎርፍ አደጋ ሥጋትን በመቀነስ፣ ለታችኛው ተፋሰስ አገራት በተለይ በድርቅ ዘመን መጠኑ ያልዋዠቀ የውኃ አቅርቦት እንዲደርሳቸው ያደርጋል ሲሉም ገልፀዋል።
ይህ የተመዘነና የተመጣጠነ የውኃ ልቀት ግብርናን፣ የኃይል የማመንጨት ሥራን፣ በቀጣናው ያለ የኃብት አጠቃቀም ምጣኔን ለማጎልበት በእጅጉ ይጠቅማልም ነው ያሉት።
የቀድሞ ሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ቡድን አባልና የውኃ ኃብት ተመራማሪው ፈቅ አሕመድ ነጋሽ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የግድቡ ሁሉም ተርባይኖች እስካሁን ወደ ሥራ መግባት የነበረባቸው ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ይህን ማድረግ አልተቻለም።
ቀደም ሲል ወደ ሥራ የገቡት ሁለት ተርባይኖችን ጨምሮ ከሰሞኑ ወደ ሥራ የገቡት ተጨማሪ ሁለት ተርባይኖች የአገሪቱን የኃይል አቅርቦት በእጅጉ እንደሚያሻሽሉት አብራርተዋል።
የሕዳሴ ግድቡ ተርባይኖች ወደ ሥራ መግባት የአገሪቷን የኃይል አቅርቦት ከማሳደግ ባለፈ ኢትዮጵያ ቀጣናውን በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር የምታደርገው ጥረት አመላካች ነው ብለዋል።
በመሆኑም ቀሪዎቹን ተርባይኖች ወደ ሥራ ማስገባት ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት ካመረተችው የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ ከሕዳሴ ግድብ የተገኘው ኃይል 17 በመቶ ድርሻ እንደነበረው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ ያመለክታል።