10 ሄክታር ማሳን ወደ ፍራፍሬ ደን የለወጡ ብርቱ አርሶ አደር - ኢዜአ አማርኛ
10 ሄክታር ማሳን ወደ ፍራፍሬ ደን የለወጡ ብርቱ አርሶ አደር
የድሬዳዋ ሕዝብ በተወለዱበት ቀዬ ስም ''ጀማል በዴሳ'' ሲላቸው የንግዱ ማኅበረሰብ ደግሞ ቀደም ብሎ በነበራቸው ጠንካራ የጫት ንግድ እንቅስቃሴ "ጀማል ቁጩ"ይላቸዋል።
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መልካ ጀብዱ አካባቢ ሰፊ ማሳ ላይ አትክልትና ፍራፍሬ የሚያለሙት እኚህ ብርቱ አርሶ አደር ትክክለኛ ስማቸው አቶ ጀማል አህመድ ዚያድ ይባላል።
ከምስራቅ ሐረርጌ ወደ ድሬዳዋ ያመሩት ጀማል አህመድ ከ12 ዓመታት በፊት 100 ፍሬ ፓፓያ በመትከል ነበር የፍራፍሬ ልማትን አሐዱ ብለው የጀመሩት።
የፓፓያውን ፍሬያማነትና ይዛላቸው የመጣውን የኢኮኖሚ ትሩፋት በማየት 15 ሺህ ፍሬ ፓፓያ በመትከል የምርት መጠናቸውን አሳድገዋል።
አርሶ አደር ጀማል በዚህ ሳይገቱ ሁሉንም ዓይነት የፍራፍሬ ዛፎች በማልማት ዛሬ ላይ ከ10 ሄክታር በላይ ማሳን በዓይነትና በብዛት የፍራፍሬ ቋሚ ተክሎች በመሸፈን ማሳቸውን ጫካ አስመስለውታል።
በተጨማርም ሰብልና የፍራፍሬ ዛፎችን እንዲሁም ስኳር ድንችን አጣምረው እያለሙ ነው።
ጥቅጥቅ ደን ከመሰለው የጀማል ማሳ ብርቱካንን ጨምሮ የፍራፍሬ ምርቶች በየቀኑ ድሬዳዋና አካባቢው ወደሚገኙ ሆቴሎችና መሰል አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በቀጥታ ይሰራጫሉ።
ለምግብነት ከሚውሉ ቋሚ ሰብሎች በተጨማሪም ለከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት የሚውሉ ልዩ ልዩ ችግኞችን በሳይንሳዊ ዘዴ በማዘጋጀትም ችግኝ ለሚፈልጉ ደንበኞቻቸው በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።
በመልካ ጀብዱ በሚገኘው የጀማል አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ለ24 ሰዎች ቋሚ የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፤ አርሶ አደሩ በዓመት ከ13 እስከ 15 ሚሊዮን ብር ገቢ እንደሚያገኙ ይገልጻሉ።
ጀማል የግብርና ኢንቨስትመንታቸውን ከድሬዳዋ ባሻገር በሌሎች የምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ለማስፋት እንቅስቃሴ ጀምረዋል።
የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና ድሬዳዋን ልክ እንደ ዱባይ የንግድ መዳረሻ የመሆን እድል ፈጥሮላታል የሚሉት አርሶ አደር ጀማል፤ ከግብርና ሥራቸው ባሻገር በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ ለመሰማራትም ፈቃድ ወስደዋል።
የግብርና ሥራቸው ሌሎች የአካባቢው በርካታ አርሶ አደሮች በአትክልትና ፍራፍሬ በማልማት የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ ምክንያት መሆናቸውን ጀማል ያነሳሉ።
በድሬዳዋና አካባቢው የከርሰ-ምድር ውኃን በአጭር ጥልቀት ቆፍሮ ማግኘት ይቻላል የሚሉት ጀማል፤ በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የውኃ ፓምፕን ጨምሮ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለማኅበረሰቡ ቢቀርቡ፤ አርሶ አደሮች ከራሳቸው አልፈው ለአገር የሚተርፍ ምርት ማግኘት እንደሚችሉ ይናገራሉ።
ከራሳቸው ጥረት ባሻገር ከከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አንስቶ በከፍተኛ አመራሮች በኩል ትልቅ ድጋፍና ዕገዛ እንደተደረገላቸው ገልጸው፤ በተለይም በግብርና ባለሙያዎች ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የግብርና፣ ውኃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ መሐመድ አሚን፤ ጀማል በራስ ተነሳሽነት ውጤታማ የሆኑ የሞዴሎች ሞዴል አርሶ አደር ናቸው ይላሉ።
በተለይም ከመደበኛ ሰብሎች ባሻገር አትክልትና ፍራፍሬ በማልማት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚቻል ማሳያ ብርቱ አርሶ አደር እንደሆኑ መስክረዋል።
ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች አርሶ አደሮች ልምድና ተሞክሯቸውን በማጋራትም ትልቅ ሚና እየተወጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከምግብ ሰብሎች ባሻገር ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ ችግኞችን በማልማት ለከተማው የራሳቸውን አበርክቶ እየተጫወቱ መሆኑን ገልፀው፤ በዚህ ዓመት ብቻ ከ100 ሺህ በላይ ችግኞችን ማዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።
ድሬዳዋ በብርቱካን፣ በመንደሪን፣ በሮማን፣ በአምበሾክና በሌሎች ፍራፍሬ ዓይነቶች በጣም የታወቀች እንደነበረች አስታውሰው፤ ከተማ አስተዳደሩ ይህን ነባር ስም ዳግም ለመመለስ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ክላስተሮች ተደራጅተው በስፋት እየለሙ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስካሁን ጀማልን የመሰሉ ከ300 በላይ አርሶ አደሮች በፍራፍሬ ምርት መሰማራታቸውን አመልክተዋል።
የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና መከፈቱ ለዚህ ተጨማሪ ዕድል መሆኑን ጠቅሰው፤ በየዓመቱ የሚመረተውን የፍራፍሬ ምርት ጥራት በማሳደግ ለውጭ ገበያ ተደራሽ ለመሆን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።