በባህር ዳር ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ በሚችል አግባብ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በባህር ዳር ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ በሚችል አግባብ እየተከናወነ ነው

ባህር ዳር፤ ነሐሴ 21/2016(ኢዜአ)፡- በባህር ዳር ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ልማትና ዕድገት ከማፋጠን ባለፈ የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ በሚችል አግባብ እየተከናወነ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።
በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ወደ ክልሎች ወርዶ እየተተገበረባቸው ካሉ ክልሎች መካከል የአማራ ክልል አንዱ ነው።
ልማቱ ከተሞችን ወደ ላቀ ምቹና ዘላቂ የመኖሪያ አካባቢ በመለወጥ፣ አረንጓዴ ልማትን በማስፋፋትና መሰረተ ልማትን በማሻሻል የህዝቡን ጤና መጠበቅ ብሎም የስራ እድል መፍጠር እንደሆነ በተግባር እየተረጋገጠ ከመጣው የአዲስ አበባ መልካም ተሞክሮ መረዳት ተችሏል።
በአማራ ክልል የኮሪደር ልማትን ተግባራዊ እያደረጉ ከሚገኙ ከተሞች መካከል የባህር ዳር ከተማ ይገኝበታል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተሻገር አዳሙ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኮሪደር ልማቱ እየተከናወነ ያለው የከተማዋን ገፅታ ከፍ በሚያደርግ አግባብ ነው።
የኮሪደር ልማቱ 22 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለው አመልክተው፤ አንደኛው ከደጅ አዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በጊዮርጊስ አሮጌውን ድልድይ አቋርጦ እስከ ገብርኤል ቤተ-ክርስቲያን ይዘልቃል ብለዋል።
ሁለተኛው ደግሞ በአዲስ አበባ መግቢያ ከመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በፓፒረስ ሆቴል አዲሱን የአባይ ድልድይ አቋርጦ እስከ ገብርኤል ቤተ-ክርስቲያን ጀርባ ከዋናው መንገድ ጋር የሚያገናኝ እንደሆነ አስረድተዋል።
የኮሪደር ልማት ስራው በተለያየ ምዕራፍ ተከፋፍሎ እንደሚከናወን ጠቅሰው፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ 1 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማት ግንባታው ሲጠናቀቅ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት በማላበስ ባህር ዳርን የበለጠ ውብና ማራኪ ማድረግ እንደሚያስችልም አብራርተዋል።
በኮሪደር ልማቱ ከአስፋልት መንገዱ ቀጥሎ ደረጃቸውን የጠበቁ የአረንጓዴ ቦታ፣ የብስክሌትና የእግረኛ መተላለፊያ መንገዶችን አካቶ እየተገነባ መሆኑን አስታውቀዋል።
የብስክሌት አሽከርካሪዎችም ሆኑ እግረኞች እንዲሁም ለጉብኝት የሚመጡ ቱሪስቶች በየተወሰኑ ርቀቶች አረፍ ብለው የሚዝናኑባቸው ቦታዎች፣ መፀዳጃ ቤቶች፣ የብስክሌትና የመኪና ማቆሚያ ቦታዎች እንዳሉትም አመላክተዋል።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ባህር ዳር ለነዋሪዎቿ ይበልጥ የተመቸች፤ ቱሪስቶች መርጠዋት የሚጎበኟትና ረጅም ጊዜ የሚቆዩቧት፣ ሳቢና ማራኪ ከተማ ትሆናለች ብለዋል።
ይህም ለከተማዋ ተጨማሪ ውበትና ገፅታ ከማላበስ ባለፈ የህዝቡን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ ዋና ስር አስኪያጁ ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማቱን ተከትሎም በተለዩ ቦታዎች የደህንነት ካሜራ እንደሚተከልም ጠቁመዋል።
የግል ባለሃብቱን፣ የልማት ድርጅቶችንና የመንግስትን ሃብት በማቀናጀት ስራውን በጊዜ ለማጠናቀቅ የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነም አስረድተዋል።
የኮሪደር ልማቱ በሚከናወንበት ወቅትና ግንባታው ሲጠናቀቅ ለበርካታ የከተማው ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል በመፍጠር በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ይሆናሉ ሲሉም ገልጸዋል።