ኮሚሽኑ በሲዳማ ክልል አጀንዳ ማሰባሰብ መርሃ ግብር ሊጀምር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ በሲዳማ ክልል አጀንዳ ማሰባሰብ መርሃ ግብር ሊጀምር ነው
ሀዋሳ ፤ ነሐሴ 21/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሲዳማ ክልል ከነገ ጀምሮ አጀንዳ የማሰባሰብ መርሃ ግብር እንደሚጀምር አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) ዛሬ በሀዋሳ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
ኮሚሽኑ ካለፈው ሰኔ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የምክክር መድረኮችን እያካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራውን በአዲስ አበባ ከተማ መጀመሩንም ተናግረዋል።
ከነገ ጀምሮ በሲዳማ ክልል ለሰባት ቀናት የሚቆይ አጀንዳ ማሰባሰብ መርሃ ግብር እንደሚጀምር ኮሚሽነር አምባዬ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።
በመርሃ ግብሩ ከክልሉ 45 ወረዳዎች የተመረጡ 900 የሚሆኑ የማህበረሰብ ወኪሎች፣ በክልሉ የሚገኙ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የተለያዩ ተቋማትና የመንግስት አካላት ተወካዮች፣ ታዋቂና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ የማህበረሰብ ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት አገራዊ መግባባት የሚፈጥሩ አጀንዳዎች በህዝባዊ ውይይት የሚሰበሰብበት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑንም ኮሚሽነር አምባዬ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ አዲስ አበባ የጀመረውን አጀንዳ የማሰባሰብ መርሃ ግብር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላና በሐረሪ ክልሎችና እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አካሂዶ ከባለድርሻ አካላት የተሰበሰቡ አጀንዳዎች መረከቡን ኮሚሽነሩ አስታውሰዋል።