የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2016 (ኢዜአ)፦ በፔሩ ሊማ በሚካሄደው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ዛሬ ይጀመራል።
በውድድሩ መክፈቻ ቀን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ሁለት የፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ።
ከሌሊቱ 7 ሰዓት ከ25 ደቂቃ የሴቶች 5000 ሜትር ፍጻሜ ይካሄዳል።
አትሌት መዲና ኢሳና አትሌት መቅደስ አለምእሸት ይወዳደራሉ።
አትሌት መዲና ከዓመት በፊት በለንደን በተካሄደው ውድድር 14 ደቂቃ ከ16 ሴኮንድ ከ54 ማይክሮ ሴኮንድ የግል ምርጥ ሰዓቷን አስመዘግባለች።
መዲና ከሁለት ዓመት በፊት በኮሎምቢያ ካሊ በተደረገው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና በ5000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ ይታወሳል።
አትሌት መቅደስ በሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም በቻይና በተከናወነ ውድድር 14 ደቂቃ ከ36 ሴኮንድ ከ70 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቷን ማስመዝገቧ ይታወቃል።
ከሌሊቱ 7 ሰዓት ከ55 ደቂቃ ደግሞ የ5000 ሜትር ወንዶች ፍጻሜ ይደረጋል። በውድድሩ ላይም አትሌት ንብረት ክንዴና አትሌት አብዲሳ ፈይሳ ይሳተፋሉ።
አትሌት ንብረት በሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም በቻይና በተካሄደ ውድድር 13 ደቂቃ ከ18 ሴኮንድ ከ97 ማይክሮ ሴኮንድ የግል ምርጥ ሰዓቱን አስመዝግቧል።
ሌላኛው ተወዳዳሪ አትሌት አብዲሳ ፈይሳ በሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም በኬንያ በተደረገ ዓለም አቀፍ ውድድር 13 ደቂቃ ከ34 ሴኮንድ ከ77 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ በመውጣት የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቱን አስመዝግቧል።
ከፍጻሜ ውድድሮቹ በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚወዳደሩባቸው የማጣሪያ ውድድሮች ይከናወናሉ።
ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ55 ደቂቃ ላይ በ800 ሜትር ሴቶች ማጣሪያ አትሌት አስቴር አሬሬ ትሳተፋለች።
አትሌት አስቴር በመጋቢት ወር 2016 ዓ.ም በጋና በተካሄደው 13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች 2 ደቂቃ ከ5 ሴኮንድ ከ5 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓት አስመዝግባለች።
አስቴር በውድድሩ ዘጠነኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።
በአምስት ምድብ ተከፍሎ በሚካሄደው የማጣሪያ ውድድር ከየምድቡ ከአንድ እስከ አራት የሚወጡ አትሌቶች በቀጥታ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ያልፋሉ። በተጨማሪም አራት ፈጣን ሰዓት ያስመዘገቡ አትሌቶች ግማሽ ፍጻሜውን ይቀላቀላሉ።
ከሌሊቱ 6 ሰዓት የ3000 ሜትር መሰናክል ሴቶች ማጣሪያ ይካሄዳል።
አትሌት ሲምቦ አለማየሁና አትሌት ፍሬህይወት ገሰሰ ይወዳደራሉ።
በምድብ 2 የምትወዳደረው አትሌት ሲምቦ በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በጣልያን በተደረገ ውድድር 9 ደቂቃ ከ00 ሴኮንድ ከ71 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምጥር ሰዓት አስመዘግባለች።
ሲምቦ በፓሪስ በተካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ3000 ሜትር መሰናክል ፍጻሜ አምስተኛ መውጣቷ ይታወሳል።
አትሌቷ በኮሎምቢያ ካሊ በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና በርቀቱ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ማግኘቷ የሚታወስ ነው።
በምድብ 2 የምትገኘው አትሌት ፍሬህይወት ገሰሰ በሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም በቻይና ሺያሜን በተካሄደ የዳይመንድ ሊግ ውድድር 9 ደቂቃ ከ25 ደቂቃ ከ53 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቷን አስመዝግባለች።
በሁለት ምድብ በሚደረገው የማጣሪያ ውድድር ከየምድቡ ከአንድ እስከ ስምንት የሚወጡ አትሌቶች ለፍጻሜ ያልፋሉ።
በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ የኢትዮጵያ አትሌቶች ትናንት በአትሌቲኮ ዴላ ቪላ ዲፖርቲቮ ናሲዮናል ስታዲየም ልምምዳቸውን አድርገዋል።
ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በ800፣1500፣ 3000 እና 5000 ሜትር በሁለቱም ጾታዎች እንዲሁም በ10000 ሜትር እርምጃ እና በ3000 ሜትር መሰናክል በሴቶች ብቻ ትወዳደራለች።
ሻምፒዮናው እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።
በውድድሩ ላይ ከ134 አገራት የተወጣጡ 1 ሺህ 720 አትሌቶች እንደሚሳተፉ የዓለም አትሌቲክስ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት በኮሎምቢያ ካሊ በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና በ6 የወርቅ፣ 5 የብርና 1 የነሐስ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎችን በማግኘት አሜሪና ጃማይካን ተከትላ 3ኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።