ቀጥታ፡

የሚዲያ ልምዶችን በመቀየርና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ረገድ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ሚና አለው - ዶክተር ወርቁ ጋቸና 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2016 (ኢዜአ)፦ የሚዲያ ልምዶችን በመቀየርና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ረገድ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩቱ ለመገናኛ ብዙኃን አመራርና ባለሙያዎች በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የሚዲያ አጠቃቀም ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀ ግብር አካሄዷል፡፡

በመርሀ ግብሩ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አመራር እና ሙያተኞች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) ዘርፉን የተመለከተ ማብራሪያ  ሰጥተዋል። 

በገለጻቸውም የሚዲያ ልምዶችን በመቀየርና አዳዲስ ነገሮችን በማስተዋወቅ ረገድ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ስላለው ሚና አብራርተዋል፡፡ 

ቴክኖሎጂው በተቋማቱ ውስጥ የሚዲያ አሰራርን ሊያዘምን በሚችልባቸው መንገዶች እና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችም በገለጻው ተዳሰዋል፡፡


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሠይፈ ደርቤ መገናኛ ብዙኃን እና ኢንስቲትዩቱ  ይበልጥ ተቀራርበው መስራት እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል፡፡ 

በዚህም የሚዲያ ዘርፉን ለማዘመን ቴክኖሎጂው የመፍትሔ ማዕከል የመሆን አቅም እንዳለውም አቶ ሠይፈ አመላክተዋል፡፡ 

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አድማሱ ዳምጠው በበኩላቸው ቴክኖሎጂው ሌላው ዓለም የደረሰበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ትልቅ ዕድል ይዞ እንደመጣ መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በየዕለት ተግባራቸው ከመጠቀም ባለፈ ለሕዝብ ለማስተዋወቅም ሚዲያዎች ትልቅ የቤት ስራ እንደሚጠብቃቸው ዋና ስራ አስፈጻሚው አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ መሳፍንት ተፈራ በበኩላቸው ቴክኖሎጂው ከይዘት ፈጠራ ጀምሮ እስከ ስርጭት ድረስ ለባለሙያዎች እገዛ እንደሚያደርግ አመላክተዋል፡፡

ይህንንም ልምድ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን አሰራር ላይ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት፡፡ 

በሚዲያ ተቋማት ውስጥ ትልቅ ችግር የሆነውን የዳታ ማከማቻ እጥረት ለመቅረፍ ኢንስቲትዩቱ እና መገናኛ ብዙኃኑ በቅርበት መስራት እንደሚገባቸው ሌላው በመድረኩ አጽንኦት የተሰጠበት ጉዳይ ነው።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) ከአመራሮቹና ባለሙያዎቹ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ገለጻ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም