የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል - ብሩክ ታዬ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል - ብሩክ ታዬ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻልና የእርካታ ደረጃን ማሳደግ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ስራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮች ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡
ዶክተር ብሩክ በውይይቱ ተቋሙ በበርካታ ስራዎች ላይ የተሻለ አፈፃፀም ያስመዘገበ ቢሆንም በደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥና በሃይል ብክነት እንዲሁም በኤሌክትሪክ ተደራሽነት ላይ ውስንነቶች ስለሚታይበት በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ምክትል ስራ አስፈፃሚ ወይዘሪት መልዕክት ሳህሉ በበኩላቸው አዲስ ሃይል በማገናኘት በኩል የተጀመረው ስራ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡
ይሁንና ሀገሪቱ ካላት ህዝብ አንጻር ሲታይ አሁን ያለው የደንበኞች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ የተለየ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ነው ያሉት፡፡
ተቋሙ የደንበኞችን የእርካታ ደረጃ ለማሳደግ በርካታ ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ሺፈራው ተሊላ ገልጸዋል፡፡
የሃይል መቆራረጥ ድግግሞሽና የሃይል ብክነት ለመቀነስ ዘመናዊ የስማርት ቆጣሪ ገጠማና የመልሶ ግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከፍተኛ አመራሮች በተቋሙ የ2016 በጀት አመት የእቅድ አፈጻፀም ላይ ውይይት በማድረግና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ በመስጠት መጠናቀቁን ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡