ቀጥታ፡

በንግዱ ዘርፍ የተደረጉ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ከአገራት ጋር የንግድ ግንኙነትን የሚያጠናክር ነው- የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2016(ኢዜአ)፦ በንግዱ ዘርፍ የተደረጉ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ዘርፉን ለማዘመንና ከአገራት ጋር የሚኖረውን የንግድ ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለፁ።

የሀገር ውስጥ የንግድ ስርዓት አበርክቶ እና ዘርፉን ማዘመን በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ”የኢትዮጵያን ይግዙ” የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፤ የሀገር ውስጥ የንግድ ስርዓትን የማጠናከር ስራ ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም ባለፉት ዓመታት የንግድ ስርዓቱን ለማዘመን የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን አስታውሰዋል።


 

በ2016 በጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ነጋዴዎች በቴክኖሎጂ የተደገፈ የንግድ ፈቃድ አገልግሎት መሰጠቱን አንስተው ዘርፉን የሚያዘምኑ የአሰራር ስልቶችና የፖሊሲ ማሻሻያዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የፖሊሲ ማሻሻያ መደረጉ የሀገር ውስጥ የንግድ ስርዓትን ከማጎልበትም ባለፈ ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚደረገውን የንግድ ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን አንስተዋል።

የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ዘመዴነህ ንጋቱ፤ የሀገር ውስጥ የንግድ ስርዓቱ ዘመኑን በዋጀ አግባብ ሳይሻሻልና ሳይዘምን በመቆየቱ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የነበሩበት መሆኑን አስታውሰዋል።


 

በመሆኑም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተደረጉ የፖሊሲ ማሻሻያዎችና የአሰራር ማሻሻያዎች ለዘርፉ እድገት ትልቅ ትርጉም ያላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አይናለም አባይነህ፤በበኩላቸው መንግስት ዘርፉን ለማሻሻል የሚወስዳቸው እርምጃዎች የንግዱ ማህበረሰብ ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ፤ አበርክቶና አቅምን የሚያጎለብቱ ስለመሆናችው አንስተዋል።


 

በቴክኖሎጂ የተደገፉ አዳዲስ አሰራሮች ለንግድ እንቅስቃሴ መጎልበት ያላቸውን ሚና በመረዳት ለገቢራዊነቱ በጋራ መስራት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።

የቤተር ቱጌዘር ማህበር ዋና ሃላፊ አባስ ሱዋበሪ፤ መንግስት ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ለመስራት ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም