ቀጥታ፡

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ተግባራት በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላሉ- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2016(ኢዜአ)፦ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ተግባራት በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥሉ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። 

በአዲስ  አበባ  ትምህርት ቢሮ የተዘጋጀው 31ኛው የትምህርት  ጉባኤ ''የላቀ  ትጋት ለትምህርት  ጥራትና ለሀገር ብልጽግና'' በሚል መሪ ኃሳብ እየተካሄደ ነው።   

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ጉባኤ በመዲናዋ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በትምህርት ዘርፉ የተከናወኑ  ተግባራት፣ የተገኙ ውጤቶችና የ2017 ዕቅዶች ላይ ውይይት ይደረጋል ተብሏል።


 

በዚሁ መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ለአገሪቷ የልማት ስኬትና የብልጽግና እቅድ ስኬት አስተማማኝ እውቀትና የሙያ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ማፍራት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

በመዲናዋ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው እነዚሁ ተግባራት በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥሉ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የትምህርት  ጥራትን ለማረጋገጥና በትውልድ የሥነ- ምግባር ግንባታ ላይ የመምህራን ድርሻ የላቀ መሆኑን አንስተው ወላጆችና አጠቃላይ የትምህርት ማህበረሰቡ እገዛ ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል። 

የትምህርት  ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ በመጽሐፍ አቅርቦትና በትምህርት ቤት ምገባ መርኃ  ግብር እንዲሁም ሌሎች ተግባራት የአዲስ አበባ ተሞክሮ ለሁሉም በምሳሌነት የሚወሰድ ነው ብለዋል።

   
 

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የሁሉም አካላት ትብብርና ጥረት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም የመምህራን አቅም ግንባታ ጉዳይ ትኩረት የሚሻ መሆኑን አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር)፤ በ2016 በጀት ዓመት ኅብረተሰቡን በማሳተፍ  6 ነጥብ  4 በሊዮን ብር ኃብት በማሰባሰብ  ለትምህርት  ሥራ ማዋል መቻሉን ጠቅሰዋል።  


 

በትምህርት  ቤት ምገባ  መርኃ  ግብር በኩልም ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ በመመደብ 779 ሺህ 231 ተማሪዎች መመገብ መቻሉን ጠቁመው በ2017 የትምህርት ዘመንም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። 

የአዲስ አበባ የመምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ድንቅዓለም ቶለሳ፤ ማህበሩ አባላቱን በማስተባበር በመጽሀፍ ዝግጅትና ሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ ላይ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የትምህርት ጥራትን የሚያረጋግጡ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ማህበሩ በትብብር እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።   

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም