ቀጥታ፡

የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪውን ይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ የባለሙያዎችን አቅም የመገንባት ሥራ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2016(ኢዜአ)፦የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪውን ይበልጥ ለማዘመንና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የባለሙያዎችን አቅም የመገንባት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከሥራቸው ባህሪ አንጻር ከመንገደኞች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ላላቸው ሠራተኞች በብሔራዊ የአየር ትራንስፖርት ፋሲሊቴሽን ፕሮግራም ዙሪያ ሥልጠና መስጠት ጀምሯል፡፡


 

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግስቴ፤ የአየር ትራንስፖርት ዘርፉ ለሀገራዊ ልማትና የምጣኔ ኃብት እድገት አበርክቶ የላቀ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪውን ይበልጥ ለማዘመንና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የዘርፉን ባለሙያዎች አቅም የመገንባት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዘርፉ የካበተ ልምድና መልካም ስም እንዳላት ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህንኑ አስጠብቆና ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

የብሔራዊ የአየር ትራንስፖርት ፋሲሊቴሽን ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ለባለሙያዎች እየተሰጠ ያለው ሥልጠናም የዚሁ ጥረት ማሳያ ስለመሆኑ አንስተዋል።

የዛሬው ሥልጠናም ከጉምሩክ፣ ኢሚግሬሽን፣ ፌደራል ፖሊስና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ለተውጣጡ ሠራተኞች መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ስምምነት የተደረገባቸውን ዝርዝር ተግባራት በላቀ ደረጃ ለመፈጸም ሥልጠናው አስፈላጊ ስለመሆኑ አንስተው፤ ይህም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

የአየር ትራንስፖርት ፋሲሊቴሽን ፕሮግራም ሥልጠናው ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚከናወን መሆኑን የወጣው መርኃ-ግብር ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም