በአማራ ክልል ለ2017 የትምህርት ዘመን ዝግጅት ተጠናቆ ምዝገባ ተጀምሯል - ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ለ2017 የትምህርት ዘመን ዝግጅት ተጠናቆ ምዝገባ ተጀምሯል - ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር)

ባህር ዳር፤ ነሐሴ 20/2016 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል ለ2017 የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን መቀበል የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቆ ምዝገባ መጀመሩን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ኃላፊዋ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) የትምህርት ዘመኑ የምዝገባ አጀማመር ሂደቱን በባህር ዳር ከተማ ትምህርት ቤቶችን ተመልክተዋል።
በ2017 የትምህርት ዘመን በዕቅድ የተያዙ ሁሉንም ተማሪዎች ምዝግቦ ለማስተማር የሚያስችል ቅድመ ሁኔታ በተቀናጀ አግባብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በማጠናቀቅም ከዛሬ ጀምሮ እስከ ነሐሴ 28 ቀን 2016 ሁሉም ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን መዝግቦ ማጠናቀቅ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በጳጉሜ ወር ደግሞ በመሸኛ የሚመጡ፣ያቋረጡና የደገሙ ተማሪዎችን በመመዝገብ እስከ መስከረም 7ቀን 2017 ዓ.ም በሁሉም ትምህርት ቤቶች ትምህርት የማስጀመር ስራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በክልሉ 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የሚያስችል የምዝገባ ስራ ዛሬ መጀመሩን አስታውቀዋል።
የመማር ማስተማሩ ስራ ውጤታማ በሆነ አግባብ እንዲከናወንም ያረጁ የመማሪያ ክፍሎችንና ወንበሮችን የመጠገንና ግቢ የማስዋቡ ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
እንዲሁም ከ16 ሚሊዮን በላይ የ1ኛና 2ኛ ደረጃ የመማሪያ መፃህፍት የማሰራጨት ስራም እየተከናወነ ሲሆን በየደረጃው ለሚገኙ የትምህርት አመራሮችና መምህራን ለመማር ማስተማሩ አጋዥ ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል ብለዋል።
በትምህርት ዘመኑ የመማር ማስተማር ሂደቱ ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
ወላጆችም በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ልጆቻቸውን በማስመዝገብና ወደ ትምህርት ቤት በመላክ የመማር ማስተማር ስራው እንዲሳለጥ መተባበር እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።
የጣና ኃይቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ሙጨ ባዘዘው እንዳሉት በመጭው የትምህርት ዘመን 5 ሺህ 148 ተማሪዎችን ለማስተማር ታቅዶ ምዝገባ ተጀምሯል።
ለዚህም እስከ ቀጣይ ሳምንት አዲስና የደገሙ፣ ያቋረጡና ከሌላ ትምህርት ቤት በመሸኛ የሚመጡ ተማሪዎችን ሙሉ በሙሉ መዝግቦ ለማስተማር በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል።
የመማር ማስተማር ስራውን በስኬት ለማካሄድም የመማሪያ ክፍሎችን የማፅዳት፣ቀለም የመቀባትና የተጎዱ የመማሪያ ወንበሮችን የመጠገን ስራም እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የስራ ሀላፊው አክለውም የዘርፉ የስራ ሃላፊዎች በፋሲሎ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ግቢ ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
በክልሉ ከ10 ሺህ 600 በላይ የአፀደ ህፃናት፣ የ1ኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማሩ ስራ መዘጋጀታቸውን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።