ኮሚሽኑ በከተማው የሙስናና ብልሹ አሠራር ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሥነ-ምግባር ግንባታ ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ በከተማው የሙስናና ብልሹ አሠራር ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሥነ-ምግባር ግንባታ ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 20/2016(ኢዜአ)፦በከተማው የሙስናና ብልሹ አሠራር ተጋላጭነትን ለመቀነስ ሕብረተሰቡን ያሳተፈ የሥነ-ምግባር ግንባታ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና በ2017 ዕቅድ ላይ ውይይት አካሂዷል።
የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም መሠረት በማድረግ በየደረጃው ላሉ የሥነ- ምግባር መከታተያ ክፍሎች የእውቅናና ሽልማት ሥነ-ሥርዓት አካሂዷል።
በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የሰላም፣ ፍትሕና መልካም አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሙሉነህ ደሳለኝ፣ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ጀማል ረዲና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ኮሚሽነር ጀማል ረዲ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተቋሙ ተልዕኮውን ሊያሳኩ የሚችሉ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ በመንደፍ በሥነ-ምግባር ግንባታና ሙስናን በመከላከል ውጤታማ ተግባራት አከናውኗል።
በሥነ-ምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል ሥልጠና መስጠት፣ ጥቆማ የመቀበልና የማጥናት፣ ሙስናና ብልሹ አሠራርን የመከላከልና የኅብረተሰቡን የሙስና ግንዛቤ ማሳደግ ላይ በትኩረት መከናወኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም የመንግሥትና የሕዝብ ኃብት ከምዝበራ የማዳንና እርምጃ የማስወሰድ አቅም ማደጉን ተናግረዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአስቸኳይና በመደበኛ የሙስና መከላከል ሥራ 3 ነጥብ 5 ቢሊየን የሚጠጋ ብር ከምዝበራ ማዳኑን ገልፀዋል።
በ2017 በጀት ዓመትም ይህን በማጠናከር በትውልድ ሥነ-ምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ተቋማት ለሙስናና ብልሹ አሠራር ተጋላጭ እንዳይሆኑ ጥናትን መሠረት ያደረገ የአሠራር ሥርዓት የማሻሻል ተግባር እንደሚከናወን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ የሀገርና የሕዝብን ንብረት ከምዝበራ ለማዳን በሚያደርገው ሂደት ሕዝቡ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የሰላም፣ ፍትሕና መልካም አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሙሉነህ ደሳለኝ በበኩላቸው፤ ኮሚሽኑ በትውልድ ግንባታና ሙስና መከላከል ስራ እያከናወነ ያለው ተግባር አበረታች ነው።
አዲስ አበባን የኢትዮጵያ ብልፅግና ተምሳሌት ማድረግ የሚቻለው ሙስናና ብልሹ አሠራርን በቁርጠኝነት በመታገል በመሆኑ፤ ሙስናን የመከላከል ሥራ በተቀናጀ አግባብ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።